በኢትዮጵያና አሜሪካ መካከል እኤአ በ2013 የተፈረመው 'ፓወር አፍሪካ' ስምምነት ተራዘመ

85
አዲስ አበባ ሰኔ 19/2010 በኢትዮጵያ ያለውን የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት ለማስፋት እኤአ በ2013 በኢትዮጵያና በአሜሪካ መካከል የተፈረመው "ፓወር አፍሪካ" ስምምነት እስከ 2020 ተራዘመ ። ስምምነቱን በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ማይክል ሬይነር እና የውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ተፈራርመዋል። ፓወር አፍሪካ ከአሜሪካ መንግስት የልማት ተራድኦ ድርጅት ጋር በመተባበር ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ አገሮች የሃይል አቅርቦት ለማሳደግ የሚሰራ ተቋም ነው። በዚህም እአአ እስከ 2030 ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገሮች ከጂኦተርማል፣ ከጸሃይ፣ ከነፋስና ሌሎች ታዳሽ ሃይሎች 30 ሺህ ሜጋ ዋት ሃይል እንዲኖራቸው እቅድ ይዟል። በኢትዮጵያ አንድ ሺህ ሜጋ ዋት ሃይል ማመንጨት የሚችል የጂኦተርማል ፕሮጀክት ከመገንባት ባለፈ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ውጤታማ የሃይል ስርጭት እንዲተገብር ሲያማክር ቆይቷል። በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ማይክል ሬይነር እንዳሉት፤ አሜሪካ በኢትዮጵያ ያለውን የሃይል አቅርቦትና ስርጭት ለማሻሻል ለኢትዮጵያ ድጋፍ ታደርጋለች። በዚህም ፓወር አፍሪካ በኢትዮጵያ የሚያከናውቸው ተግባራት ቀጣይነት እንዲኖራቸውና የግል ባለሃብቶች ዘርፉን ማሳደግ እንዲችሉ ስምምነቱን እአአ እስከ 2020 ማራዘማቸውን ገልጸዋል። ኢትዮጵያ የአፍሪካ የኤሌክትሪክ ሃይል ማማ መሆኗን የገለጹት አምባሳደሩ፤ በኢትዮጵያና በአካባቢው የአፍሪካ አገሮች በቂ የሃይል አቅርቦትና ስርጭት እንዲኖር ለመደገፍ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል። የውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በበኩላቸው፤ ፓወር አፍሪካ ከሰሃራ በታች ባሉ አገሮች ያለውን የኤሌክትሪክ አቅርቦት ለማሻሻል የሚያደርገውን ድጋፍ አድንቀዋል። ስምምነቱ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን የንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ለማጎልበት ኢትዮጵያ በግል ዘርፉ እንዴት ውጤታማ መሆን እንዳለባት አቅም ለመፍጠር የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል። በተመሳሳይ በአሜሪካ ምክትል የንግድ ሚኒስትር ጊልበርት ካፕላን የሚመራው የልዑካን ቡድን በኢትዮጵያ ያደረገውን ውይይት አጠናቆ መግለጫ ሰጥቷል። ምክትል የንግድ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ የሚሰማሩ የግል ባለሃብቶች በአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ለውጥ እንዲያመጡ አሜሪካ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ታደርጋለች። በኢትዮጵያ በነበራቸው የሁለት ቀናት ቆይታ በተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፍ በጋራ ለመስራት የሚያስችል ስምምነት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም