በምስራቅ ጎጃም ዞን የ115 ያለ እድሜ ጋብቻን እንዲቋረጥ አደረገ

125
ደብረማርቆስ ኢዜአ ጥር 29 ቀን 2012 ዓ.ም በምስራቅ ጎጃም ዞን ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በተደረገ ርብርብ የ115  ያለእድሜ ጋብቻን   እንዲቋረጥ ማደረጉን የዞኑ ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ መምሪያ ገለፀ ። በዞኑ እንደ ባህል ተወስዶ ሲፈጸም የነበረው የሴት ህጻናት ያለእድሜ ጋብቻ ባለፉት አምስት ዓመታት እየቀነሰ መምጣቱ ተገልፇል ። በመምሪያው የሴቶች ንቅናቄና ተሳትፎ ማስፋፊያ ቡድን መሪ አቶ ዳግማዊ ገበየሁ ለኢዜአ እንደገለጹት ያለእድሜ ጋብቻ በሴት ልጆች ላይ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር የሚያስከትል ድርጊት ነው። ችግሩን ለማስቆም በተረደገ ርብርብም በግማሽ ዓመቱ ለእድሜ ልኬታ ምርመራ ከቀረቡት 555 ሴት ህጻናት መካከል 115 ሴት ህጻናት እድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች ሆኖ በመገኘቱ ጋብቻቸው እንዲቋረጥ ተደርጓል። ጋብቻውን ለማቋረጥ የተቻለውም የጎጂ ልማዳዊ ድርጊት አስወጋጅ ኮሚቴዎች፣ የሴት አደረጃጀቶች፣ የአካባቢው ተማሪዎችና መምህራን በሰጡት ጥቆማ መሰረት ተገቢውን ክትትል በመደረጉ ነው። መስሪያ ቤቱ ከፍትህ አካላት፣ ከጤና ባለሙያዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በተካካሄደው  ሁሉን አቀፍ ጥረት ባለፉት አምስት ዓመታት ያለእድሜ ጋብቻ እየቀነሰ መምጣቱን አስረድተዋል። በቀጣይም ያለእድሜ ጋብቻ በሴት ልጆች ላይ የፌስቱላ ተጋላጭነትን በመጨመር ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ የሚፈጥር በመሆኑ ለህብረተሰቡ ዘንድ ተከታታይ ግንዛቤ ለመፍጠር በትኩረት ይሰራል ብለዋል። በደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህርና ተመራማሪ አቶ አለሙ ታየ በበኩላቸው ከሁለት ዓመት በፊት በሸበል በረንታና በባሶሊበን ወረዳ ባካሄዱት ጥናት ያለእድሜ ጋብቻ አሁንም መሰረታዊ ችግር ነው። ለዚህም የፈጻሚ አካላት ቁርጠኝነት ማነስ፣ የህክምና ምርመራው ዘመናዊ አለመሆን፣ የህብረተሰቡ ግንዛቤ እያደገ ቢመጣም ከልማዳዊ አስተሳሰብ አለመውጣትና  ሌሎች ችግሮች በመኖራቸው ነው ብለዋል። ጋብቻቸው ከተቋረጠላቸው ህጻናት መካለል የደጀን ወረዳ የቆንቸር ቀበሌ ነዋሪ ተማሪ  እመናት ያዜ እንዳለችው “ያለፍላጎቴ ሊፈጸምብኝ የነበረው ጋብቻ በመቋረጡ ተደስቻለሁ” ስትል ገልጻለች። ጥር መጀመሪያ አካባቢ ሊድሩኝ መሆኑ በመሰማቱ አባቴና እናቴ ቀበሌ ድረስ ተገደው በመቅረብ ጋብቻውን እንዲያቋርጡ ፈርመው ተመልሰዋል ብላለች ። እኔም “የሚድሩኝ መሆኑን ስሰማ በተፈጠረብኝ ጭንቀት ትምህርቴን ለመከታተል ተቸግሬ ነበር ያለችው ወጣቷ ጋብቻው መቋረጡን ከሰማሁ ወዲህ ግን ከሃሳብና ጭንቀት ነጻ በመሆን ትምህርቴን መከታተል ችያለሁ” የሚል አስተያየት ሰጥታለች ። የጎዛምን ወረዳ የአባሊባኖስ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ይስማው ገብሬ እንዳሉት ደግሞ ወላጆች  ሴት ልጃቸውን እድሜያቸው ሳይደርስ የሚድሩት "ቆማ ቀረች " የሚለውን ስድብና አሽሙር በመፍራት መሆኑን ገልፀዋል ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም