በተፈጥሮ ሃብት የደን አስተዳደር ስርዓት ለ6 ሺህ ወጣቶች የስራ እድል ተፈጥሯል

92
ጎንደር ኢዜአ ጥር 29 ቀን 2012 ዓ.ም  በምዕራብ ጎንደር ዞን በተፈጥሮ ሃብት አሳታፊ የደን አስተዳደር ስርዓት ከስድስት ሺህ ለሚበልጡ ወጣቶች የስራ እድል መፈጠሩን የዞኑ ግብርናና ገጠር ልማት መምሪያ ገለፀ ፡፡ በመምሪያው የአካባቢ ህግ ተከባሪነትና የአካባቢ ማህበረሰብ ተፅዕኖ ግምገማ ቡድን መሪ አቶ ሀብታሙ አድጎ እንደተናገሩት ለወጣቶቹ  የስራ እድል የተፈጠረው መተማና ቋራ ወረዳዎች ነው፡፡ የስራ እድሉ የተፈጠረው  በ35 ማህበራት ለተደራጁ ወጣቶች ሲሆን 180 ሺህ ሄክታር የተፈጥሮ ደን ጠብቀውና ተንከባክበው እንዲጠቀሙ በማድረግ ነው። ወጣቶቹ በተሰጣቸው የደን ሃብት እጣንና ሙጫ አምርቶ ለገበያ በማቅረብ እንዲጠቀሙ እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል። ከደን ሃብቱም በዓመት ከ11 ሺህ ኩንታል በላይ የእጣንና ከ7 ሺህ ኩንታል በላይ ሙጫ በማምረት ከምርት ሽያጭ ከፍተኛ ገቢ እያገኙ መናቸውን ተናግረዋል። ከእጣንና ሙጫ ምርት በተጨማሪም በሌሎች የደን ውጤቶች እየተጠቀሙ እንደሆነም አመልክተዋል። የደን ሀብቱን በመጠበቅና በማልማት የበለጠ ተጠቃሚ እንዲሆኑና ለሌሎች ወጣቶችም የስራ እድል መፍጠር ይቻል ዘንድ ለማህበራቱ አባላት የተለያዩ ቴክኒካዊ ድጋፎች እየተሰጠ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ማህበራቱ በአሳታፊ የደን አስተዳደር ከተረከቡት የደን ሀብት በተጨማሪ ሌሎች የደን ይዞታዎች ላይ የሚደረግን የደን ጭፍጨፋና ህገ-ወጥ የደን ውጤቶች ዝውውር የመከላከል ስራ እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰዋል። በመተማ ወረዳ የዳስ ጉንዶ ዘላቂ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ማህበር ሰብሳቢ ወጣት ጓንቸ ተበጀ በበኩሉ 178 ሆነው በመደራጀት 5 ሺህ 200  ሄክታር የሚሸፍን ደን ተረክበው እየጠበቁና እየተንከባከቡ መሆኑን ተናግሯል። እጣን ማምረት የጀመሩት ባለፈው ጥቅምት ወር መሆኑን ጠቅሶ እስከ አሁንም 450 ኩንታል እጣን ማምረት እንደቻሉ ተናግሯል። ከሰበሰቡት የእጣትን ምርት ሽያጭም 3 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገቢ ማግኘት እንደቻሉ አውስቶ በዓመት በትርፍ ክፍፍል ከ30 ሺህ ብር በላይ ገቢ እንደሚያገኙ ገልጿል። በደኑ ካመረቱት የእጣንና ሙጫ ምርት በተጨማሪ የደን ሃብቱን ከጥፋት መጠበቅ ችለናል ያለው ደግሞ በቋራ ወረዳ የበደላ ዘላቂ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ማህበር ሰብሳቢ አስማረ ሙላት ነው፡ ማህበሩ 164 አባላት ያሉት ሲሆን  500 ኩንታል እጣንና 180 ኩንታል ሙጫ በማምረት 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ሽያጭ መፈፀማቸውን ተናግሯል፡፡ 5 ሺህ ሄክታር ደን ተረክበው እያስተዳደሩ መሆኑን ገልጾ በባለቤትነት ከያዙት ደን በተጨማሪ በአካባቢው ያሉ የወል መሬት ደኖችን በመጠበቅ ላይ እንደሚገኙ ተናግሯል፡፡ በዞኑ 623 ሺህ 200 ሄክታር የደን ሽፋን ያለው ሲሆን ከጠቅላላለው የዞኑ ቆዳ ስፋትም 40 በመቶ የሚጠጋ መሆኑን ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም