የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ሙሐመዱ ቡሐሪ በኢትዮጵያ የስራ ጉብኝት ያደርጋሉ

68
ጥር 29/2012 (ኢዜአ) ለአፍሪካ ህብረት 33ኛው የመሪዎች ጉባኤ አዲስ አበባ ዛሬ የሚገቡት የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ሙሐመዱ ቡሐሪ በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ያደርጋሉ። ፕሬዚዳንቱ የካቲት 1 እና 2 ቀን 2012 ዓ.ም በሚካሄደው 33ኛው የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ለመሳተፍ ዛሬ አዲስ አበባ እንደሚገቡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነቢያት ጌታቸው ለኢዜአ ገልጸዋል። ሙሐመዱ ቡሐሪ በመሪዎች ጉባኤ ከተሳተፉ በኋላ በማግስቱ በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት እንደሚኖራቸው ታውቋል። ፕሬዚዳንቱ ዛሬን ጨምሮ በኢትዮጵያ የአምስት ቀን ቆይታ ይኖራቸዋል። ፕሬዚዳንቱ በቆይታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድና ከሌሎች የመንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር የአገራቱ የሁለትዮሽ ግንኙነት በሚያጠናክሩበትና በጋራ በሚሰሩባቸው ጉዳዮች ላይ ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል። በተጨማሪም ሙሐመዱ ቡሐሪ በኢትዮጵያ ከሚገኙ የናይጄሪያ ማህበረሰብ አባላት ጋር ውይይት እንደሚያደርጉም ይጠበቃል። ከፕሬዚዳንቱ ጋር ሌሎች ዘጠኝ የናይጄሪያ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት እንደሚመጡ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም