የአማራ ክልል ገቢ እያደገ መጥቷል

55
አዲስ አበባ፣ጥር 29/2012 (ኢዜአ) በአማራ ክልል የግብር ስርዓቱን በማዘመን በተካሄደ የህግ ማስከበር ስራ የሚሰበሰበው ገቢ እያደገ መምጣቱን የክልሉ ገቢዎች ቢሮ አስታወቀ። በቢሮው የግብር አወሳሰንና ክትትል ዋና የስራ ሂደት ዳይሬክተር አቶ ይታይህ ፈንቴ ለኢዜአ እንደገለጹት ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ግብር ለመሰብሰብ ጠንካራ ህግ የማስከበር ስራ እየተከናወነ ነው። በዚህ ዓመት በተካሄደ የህግ ማስክበር ስራም 174 ነጋዴዎች ያለደረሰኝ ግብይት ሲፈጽሙ እጅ ከፈንጅ በመያዛቸው እያንዳንዳቸው 50 ሺህ ብር እንዲቀጡ ተደርጓል። በተጨማሪም  ዘጠኝ ነጋዴዎች በህግ ጥላ ስር ውለው ጉዳያቸው  በህግ እየታየ ሲሆን አንድ ሺህ 550 የሚሆኑት ነጋዴዎች ደግሞ ከከፍተኛ እስከ ዝቅተኛ ማስጠንቀቂያ የተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል። በተሰራው ህግ የማስከበር ስራም በዚህ በጀት ዓመት ለመሰብሰብ ከታቀደው 14 ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር ውስጥ በግማሽ ዓመቱ ከስድስት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር በላይ ማሳካት መቻሉን አቶ ይታይህ አብራርተዋል። በግማሽ ዓመቱ የተሰበሰበው ገቢም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በአንድ ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር  ብልጫ እንዳለው ገልፀዋል። ኢኮኖሚው እያመነጨ ያለውን ገቢም በመሰብሰብ የክልልን ዓመታዊ ወጭ ከ25 እስከ 27 በመቶ መሸፈን እንደተቻለ ጠቁመዋል። በቀሪ ወራትም የተቀመጠውን እቅድ ሙሉ በሙሉ ለማሳካት ጠንካራ የግንዛቤ ፈጠረና የህግ ማስከበር ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል። ክልሉ ያለውን ገቢ የመሰብሰብ አቅም ሙሉ በሙሉ እንዲያሳካም ነጋዴዎች ህዝብና መንግስት የጣለባቸውን ሃላፊነት መወጣት እንዳለባቸውም ጠይቀዋል። በህዝቡ ዘንድ እያደገ የመጣውን የልማት ጥያቄ ለማሳካትም ግብር በተሟላ መንገድ ለመሰብሰብ የሚደረገውን ጥረት ህገ ወጥ ነጋዴዎችን በማጋለጥ ህብረተሰቡ የድርሻውን እንዲወጣም አቶ ይታይህ አሳስበዋል። በጣና ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ሰናይት ብዙነህ እንዳሉት በሸቀጣሸቀጥ ንግድ ስራ በመሰማራት የራሳቸውንና የቤተሰባቸውን ህይወት በመምራት ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል። መንግስት የሚያቀርባቸውን የፍጆታ እቃዎችና ሌሎች የኢንዱስትሪ ውጤቶችን በመሸጥ ከሚያገኙት ገቢ በዚህ ዓመት ከአራት ሺህ ብር በላይ ግብር በወቅቱ መክፈላቸውን ተናግረዋል። በቀበሌ 14 አራት በመጠጥና ምግብ ንግድ የተሰማሩት አቶ ደረበ ደጉ በበኩላቸው ለመንግስት የሚከፈል ግብር አገርን ለማልማትና ለማሳደግ እንደሚውል አሁን ላይ አካባቢያችን በመለወጡ መገንዘብ ችያለሁ ብለዋል። "በየዓመቱ የግብር መክፈያ ጊዜው ሲደርስ የሂሳብ መዝገቤን በማስመርመርና ኦዲት በማስደረግ የሚጠበቅብኝን ግብር እከፍላለሁ፤ በዚህ ዓመትም ከ11 ሺህ ብር በላይ ከፍያለሁ" ብለዋል። ግብርን በወቅቱ መክፈላቸው ከተጨማሪ እንግልትና ቅጣት ራሳቸውን እንዲጠብቁ እንዳደረጋቸው አስተያየት የሰጡት ግብር ከፋዮች ገልጸዋል። ባለፈው ዓመትም ከ11 ነጥብ አንድ ቢሊየን ብር በላይ ገቢ በመሰብሰብ ለልማት ማዋል መቻሉ የሚታወስ ነው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም