የጀርመን ሥመ-ጥር የተሽከርካሪና መሰል ኩባንያዎችን ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት እየተሰራ ነው - አምባሳደር ብሪታ ዋግነር

93
አዲስ አበባ ጥር 28/2012 (ኢዜአ) ተሽከርካሪና የተሽከርካሪ አካላት የሚያመርቱ የጀርመን ኩባንያዎችን ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በቅርበት እየሰሩ መሆኑን በኢትዮጵያ የአገሪቷ አምባሳደር ብሪታ ዋግነር ገለጹ። በቅርቡ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የተደረሰውን የ'ሪፎርም ትብብር' የስምምነት ማዕቀፍ ተግባራዊ ለማድረግ ጀርመን በቅርበት እየሰራች መሆኑንና አጋርነቱ መጠናከሩን ጠቁመዋል። በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ብሪታ ዋግነር እንደተናገሩት የሁለቱ አገራት ግንኙነት እያደገ መጥቷል፤ በኢትዮጵያ የመጣውን ለውጥ ተከትሎም ተጠናክሯል። በቅርቡ በአገራቸው የኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴርና በኢትዮጵያ የፋይናንስ ሚኒስቴር መካከል የተደረሰው የ'ሪፎርም ትብብር' ለውጡን ለመደገፍ ያለመ መሆኑን ገልጸዋል። ይህንንም ተከትሎ ኢትዮጵያ ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢ ለመፍጠር የምታደርገውን ጥረት በመደገፍ የጀርመን ግዙፍ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ እየሰሩ መሆኑን ነው ያመለከቱት። በዚህና በሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች ላይ የሁለቱ አገራት የዘርፉ ባለሙያዎችም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተከታታይ ወይይት እያደረጉ መሆኑን አምባሳደር ዋግነር ተናግረዋል። በቅርቡ ግዙፉ የቮልስ ዋገን መኪና አምራች ኩባንያ ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ያደረገውን ጥረት የሪፎርም ትብብሩ አካል መሆኑን ገልጸው ሌሎችም ተዛማች ኩባንያዎች እንዲመጡ በር ይከፍታል ብለዋል። ሌሎችም በርካታ ግዙፍ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ እየመጡ ያለውን ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታ እያጠኑና ከመንግሥት ባለሥልጣናትን ጋር እየተወያዩ መሆኑን ጠቁመዋል። አገራቸው በኢትዮጵያ የቴክኒክና ሙያ ተቋማትን ጠንካራ ለማድረግ የሚደረገውን አገራዊ ጥረት ከግብ ለማድረስም ሙያዊ ድጋፍ እያደረገች መሆኗን ጠቁመዋል። ይህም በዓለም አቀፍ የልማት የትብብር ኤጀንሲ GIZ በኩል እየተፈጸመ መሆኑንና በርካታ የዘርፉ  አሰልጣኞች በጀርመን ባለሙያዎች መሠልጠናቸውን ጠቅሰዋል። በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ትብብሩን ለማጠናከር የአጋርነት ሥምምነት መፈረሙን ገልጸው ይህም በነጻ የትምህርት ዕድል ተጠናክሯል ነው ያሉት። ከአንድ ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያን ተማሪዎች በጀርመን ዩኒቨርሲቲዎች የትምህርት ዕድል ማግኘታቸውንም ጠቁመዋል። በሌላ በኩል የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎችን በተመጋገበ መልኩ እየሰሩ መሆኑን አምባሳደሯ ተናግረዋል። በቅርቡ የኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ለኢትዮጵያ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ለሥልጠና የሚጠቅሙ ዘመናዊ የግብርና ማሽነሪዎችን ማስረከባቸውን ገልጸዋል። በባሌ ብሔራዊ ፓርክና በሰሜን ተራሮች አካባቢ የተፈጥሮ ኃብትን የመንከባከብ ሥራ እንዲሁም በጣና ሀይቅ ብዝኃ ህይወትንና የውኃ ኃብትን የመንከባከብ ሥራን እንደግፋለን ብለዋል። በኢትዮጵያ የሚካሄደውን ምርጫ ፍትሃዊና ተዓማኒ ለማድረግ እንዲቻል የሚካሄደውን የአቅም ግንባታ ለማገዝ በአውሮጳ ኅብረት በኩል 10 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል። ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ሠላምና ደኅንነት እንዲረጋገጥ የምታደርገውን የተናጠልና የጋራ ጥረቶች ጀርመን በአድናቆት እንደምታየውና ድጋፏንም አጠናክራ እንደምትቀጥል ጠቁመዋል። የኢትዮጵያና የጀርመን የሁለትዮሽ ግንኙነት የተጀመረው በ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ላይ ሲሆን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ይበልጥ እየተጠናከረ መጥቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም