በኢትዮጵያና አካባቢዋ የተከሰተው የአንበጣ መንጋ እፅዋቶችን ሙሉ በሙሉ የማጥፋት አቅም አለው - ፋኦ

68
አዲስ አበባ ጥር 28/2012 (ኢዜአ) በኢትዮጵያና አካባቢዋ የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ በተጠናከረና በተቀናጀ መንገድ መከላከል ካልተቻለ እፅዋቶችን ሙሉ በሙሉ የማጥፋት አቅም እንዳለው የዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት  /ፋኦ/ አሳሰበ። ድርጅቱ በኢትዮጵያ የአንበጣውን መንጋ ለመከላከል 40 ሚሊዮን ዶላር እያሰባሰበ መሆኑን አስታውቋል። በፋኦ የኢትዮጵያ የተባይ መከላከል ኤክስፐርት ዶክተር ባየህ ሙላቱ ለኢዜአ እንደገለጹት በአገሪቷና በአካባቢዋ የተከሰተው የአንበጣ መንጋ በእፅዋት ላይ ከፍተኛ ጥፋት የማድረስ አቅም አለው። ድርጅቱ አስፈላጊውን የቴክኒክ ድጋፍ በማድረግና ሃብት በማሳባሰብ ለግብርና ሚኒስቴር ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል። ከለጋሽ አገራትና ደጋፊዎች 15 ሚሊዮን ዶላር ቃል መገባቱንና ከዚሁ ውስጥ ገቢ እየተደረገ እንደሆነም ጠቁመዋል። ከዚህ ቀደም አገራት ለጉዳዩ ብዙም ትኩረት ባለመስጠታቸው የገንዘብ ድጋፉም በዛው ልክ የተቀዛቀዘ ነበር ነው ያሉት ዶክተር ባየህ። ባለፉት ጊዜያት የኢትዮጵያ መንግስት ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር ከፍተኛ ሃብት በመመደብ የሰራው ስራ የአንበጣ መንጋው ሊያስከትለው የሚችለውን ጉዳት ቀንሷል። በአንድ ስኩዬር ኪሎ ሜትር ከ20 እስከ 120 ሚሊዮን የሚጠጋ አንበጣ ይፈለፈላል። በአፋር ክልል በ500 ስኩዬር ኪሎ ሜትር ቦታ ላይ ቁጥጥር ተደርጎ በትሪሊዮን የሚቆጠሩ አንበጦች መገደላቸውንና ይህ ባይሆን ኖሮ ከፍተኛ ጉዳት ይደርስ እንደነበረ ገልጸዋል። አሁን ባለው አቅም እየተከሰተና ከሌሎች አገራትም እየገባ ያለውን የአንበጣ መንጋ ለመከላከልና ለመቆጣጠር አስቸጋሪ ስለሆነ የአገራት ድጋፍ ወሳኝ ነውም ብለዋል። በቂ የመድሃኒት መርጫ አውሮፕላንና ሃብት፣ የሰው ኃይልና የአገራት ትብብር አነስተኛ መሆን ችግሩን ሊያባብሰው ይችላል የሚል ስጋት እንዳለም ጠቁመዋል። በቀጣይም ከውጭ የሚገባውና በአገር ውስጥ የሚፈለፈለው የአንበጣ መንጋ የሚያደርሰው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን ትንበያዎች ከወዲሁ አመላክተዋል። በበቂ ሁኔታ መከላከል ካልተቻለ ኢትዮጵያ በምግብ እህል ሯሷን ለመቻል የምታደረገውን ጥረት ከመጉዳት ባለፈ እፅዋቶቿን ሙሉ በሙሉ በማጥፋት በሰውና በእንስሳት ሕይወት ላይ የከፋ ጉዳት ያስከትላል ብለዋል። የአገራት ትብብር መጠናከር እንዳለበት የጠቆሙት ዶክተር ባየህ በተለይ ኢትዮጵያ ከሶማሌና ከአጎራባች አገራት እየተፈለፈሉ የሚመጡ አንበጦችን ለማከላከል በቂ ትኩረት መስጠት አለባት ነው ያሉት።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም