የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከሩዋንዳ አቻቸው ጋር ተወያዩ

138
አዲስ አበባ፣ጥር 28/2012 ዓ/ም (ኢዜአ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው እና የሩዋንዳ የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ዶክተር ቪንሰንት ቢሩታ በአገራቱ የጋራ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል። አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የሩዋንዳ አቻቸውን በጽህፈት ቤታቸው ባነጋገሩበት ወቅት የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ሆነው በመሾማቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸውላቸዋል። በሚኒስትርነት ዘመናቸው የሁለቱ አገራት ግንኙነት ይበልጥ እንደሚጠናከር እምነታቸው መሆኑንም ገልፀውላቸዋል። ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ በሕዳሴው ግድብ ውሃ ሙሌትና አለቃቀቅ ዙሪያ በቅርቡ ያደረጉትን ውይይት በተመለከተም አቶ ገዱ ለሩዋንዳው አቻቸው ገለጻ አድርገዋል። ዶክተር ቪንሰንት ቢሩታ በበኩላቸው ኢትዮጵያና ሩዋንዳ ጠንካራ የሁለትዮሽ ግንኙነት እንዳላቸው በማንሳት አገራቱ በሁለትዮሽ፣ በአፍሪካ ኅብረትና በሌሎችም ዓለም አቀፍ መድረኮች በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ በሩዋንዳ ጉብኝት እንደያደርጉም ዶክተር ቪንሰንት ግብዣ አቅርበውላቸዋል። ሁለቱ ሚኒስትሮች የአገራቱን ግንኙነት ለማጠናከር ይረዳ ዘንድ ያቋቋሙት የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ በቅርቡ እንዲካሄድም ተስማምተዋል። ዶክተር ቪንሰንት የሩዋንዳ የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር በመሆን በሕዳር 2012 ዓ.ም መሾማቸው ይታወቃል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም