በመጪው የመኸር ምርት ዘመን ከ13 ሚሊዮን ሄክታር በላይ የእርሻ መሬት በተለያዩ ሰብሎች ለመሸፍ ታቅዷል

58
አዲስ አበባ ሰኔ19/2010 በመጪው የመኸር ምርት ዘመን ከ13 ሚሊዮን ሄክታር በላይ የእርሻ መሬት በተለያዩ ሰብሎች ለመሸፈን እቅድ ተይዞ አስፈላጊው እንቅስቃሴ መጀመሩን የግብርናና እንስሳት አብት ሚኒስቴር አስታወቀ። ምርትና ምርታማነትን ከ30 በመቶ በላይ ለማሳደግ የሚያስችል የግብዓት አቅርቦት መዘጋጀቱንም ሚኒስቴሩ ገልጿል። ያለፈው ዓመት የግብርና ምርትና ምርታማነት መጠን ከእቅዱ በታች እንደሆነ ይነገራል። ለዚህም አንዱ ምክንያት የምርት ግብአቶች በተለይም የምርጥ ዘር አቅርቦት ባለፉት ሶስት ዓመታት ደካማ እንደሆነ የፕላን ኮሚሽን መግለጹ ይታወሳል። ዘንድሮ ግን የዚህ ዓይነቱ ችግር እንዳይፈጠር አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ነው ሚኒስቴሩ ያመለከተው። የአፈር ማዳበሪያ፣ ምርጥ ዘርና ሌሎች ቴክኖሎጂዎችን ጨምሮ ለግብርና ምርትና ምርታማነት ወሳኝ ለሆኑት ግብአቶች ዝግጅት ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቷል ተብሏል። ዘንድሮ ከ370 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰብ እንዲቻል 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታል ምርጥ ዘርና 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የአፈር ማዳበሪያ መዘጋጀቱን የሚኒስቴሩ ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ አቶ አለማየሁ ብርሃኑ ለኢዜአ ገልፀዋል። እንደ አቶ አለማየሁ ገለጻ፤ በምርት ዘመኑ ከ13 ሚሊዮን ሄክታር በላይ የእርሻ መሬት በተለያዩ ሰብሎች ለመሸፍ እቅድ ተይዞ አስፈላጊው እንቅስቃሴ ተጀምሯል። የተለያዩ የምርጥ ዘር ዓይነቶች ከወዲሁ ለአርሶ አደሩ መቅረብ መጀመራቸውንም አቶ አለማየሁ ተናግረዋል። የአርሶ አደሩ የአፈር ማዳበሪያ ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን የሚጠቅሱት ዳይሬክተሩ ከጀቡቲ ወደብ የሚገባው ማዳበሪያ በመላው አገሪቱ ወደ ተዘጋጁት 123 ያህል መጋዘኖች በቀጥታ የሚገባ በመሆኑ አርሶ አደሩ የሚፈልገውን ማዳበሪያ ማግኘት እንደሚቻልም አስረድተዋል። ከዚህ በፊት ከማዳበሪያ ግዥ ጋር በተያያዘ ይታይ የነበረውን መጓተት ማስወገድ እንዲቻል ቀደም ብሎ እንዲገዛና ወደ አገር ውስጥ እንዲገባ መደረጉን ተናግረዋል። መኸር አምራች በሆኑ የአገሪቱ ክፍሎች በአሁኑ ወቅት ያለው የዝናብ ስርጭት ሁኔታ ጥሩ መሆኑን የገለፁት አቶ አለማየሁ ይህም  ከታቀደው በላይ ምርት ለመሰብሰብ እንደሚያግዝ ጠቅሰዋል። ዝናቡ በአንዳንድ አካባቢዎች ከመጠን በላይ ሊሆን እንደሚችልና ጎርፍም እንደሚያስከትል በመገንዘብ በእነዚህ አካባቢዎች ያለው ህብረተሰብ እንዲጠነቀቅ የሚያስችለውን መረጃ እንዲያገኝ እየተደረገ ነው ተብሏል። የዝናብ እጥረት በሚያጋጥማቸው የአርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች ደግሞ የዝናብ ውሃን የማቆርና የማጠራቀም ስራ እንዲከናወን እየተደረገ መሆኑንም የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ ገልፀዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም