በቻይና የሚኖሩ ኢትጵያዊያንን እና የውጭ ዜጎችን  ደህንነት ለመጠበቅ አስፈላጊው ጥንቃቄ እየተደረገ ነው

80
ጥር 26/2012 (ኢዜአ) የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት እየተደረገ ባለው እንቅስቃሴ ኢትዮጵያ እያደረገች  ያለውን ድጋፍ የቻይና ውጭ ጉዳይ  ረዳት ሚኒስትር  ቼን ሽያዶነግን አመሰገኑ፡፡ በቻይና የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንን እና የውጭ ዜጎችን  ደህንነት ለመጠበቅ አስፈላጊው ጥንቃቄ እና ድጋፍ እየተደረገ መሆኑንም ቼን ጠቅሰዋል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሂሩት ዘመነ የቻይና ውጭ ጉዳይ  ረዳት ሚኒስትር  ቼን ሽያዶነግን ዛሬ በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡ ወይዘሮ ሂሩት ከረዳት ሚኒሰትሩ ጋር በነበራቸው ቆይታ በሁለትዮሽ  እና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል። ሁለቱ ሀገሮች በዓለም አቀፍ መድረኮች የሚያደርጉትን ግንኙነት አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ በአሁኑ ስዓት በቻይና የተከሰተውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለመቆጣጠር ቻይና ሙሉ አቅም እና ብቃት እንዳላት ኢትዮጵያ እምነቷ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡ ወረርሽኙ ዓለም አቀፍ የጤና ስጋት በመሆኑ ኢትዮጵያ እንደ ወትሮዋ ሁሉ ከቻይና ጎን በመቆም ወረርሽኙን ለመከላከል አስፈላጊውን ትብብር እንደምታደርግም አረጋግጠዋል። የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የዓለም የጤና ድርጅት ባስቀመጠው መመሪያ መሰረት ኢትዮጵያ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እያደረገች መሆኗንም ወይዘሮ ሂሩት ገልጸዋል። የቻይና ውጭ ጉዳይ ረዳት ሚኒስትር ቼን ሽያዶነግ በበኩላቸው ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ላላት ግንኙነት ልዩ ትኩረት እንደምትሰጥ በመግለጽ፤ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት እየተደረገ ባለው እንቅስቃሴ ኢትዮጵያ እያደረገች ያለውን ድጋፍ አድንቀዋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ለቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ዥንፒንግ ያስተላለፉትን መልዕክት በማንሳት ምስጋናቸውን አቅርበዋል። የቻይና መንግስት የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት እና ለመቆጣር አገር አቀፍ ስርዓት መዘርጋቱን ብሎም በሽታውን ለመቆጠጣር የሚያስችል ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ገልጸው፣ቻይና ከዓለም  መንግስታት እና ከዓለም የጤና ድርጅት ጋር በጋራ እየሰራች መሆኑን አንስተዋል፡፡ በቻይና የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንን እና የውጭ ዜጎችን  ደህንንት ለመጠበቅ አስፈላጊው ጥንቃቄ እና ድጋፍ እየተደረገ መሆኑንም ረዳት ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡ በሁለቱ አገሮች ትብብር እየተከናወኑ ያሉ በርካታ ፕሮጀክቶች በውጤት እንዲጠናቀቁ አስፈላጊው ክትትል እና ድጋፍ እንደሚደረግም ቼን አረጋግጠዋል። ሁለቱ አገሮች በቻይና አፍሪካ ትብብር፣ በተባበሩት መንግስታት እና ሌሎች ዓለም  አቀፍ መድረኮች የሚያደርጉትን ግንኙነት አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልጸዋል። ኢትዮጵያ እና ቻይና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩበትን 50ኛ ዓመት ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ  ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም