ለም አካባቢን ለትውልድ ለማስተላለፍ ጥረታችንን አጠናክረን እንሰራለን--የቤንሻንጉል ጉሙዝ አርሶአደሮች

79
አሶሳ ፣ ጥር 26/2012 ዓ.ም (ኢዜአ) በተፋሰስ ልማት ባገኙት ውጤት የለማ አካባቢን ለትውልድ ለማስተላለፍ የጀመሩትን ጥረት አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አንዳንድ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አርሶ አደሮች ተናገሩ፡፡ በክልሉ ለሁለት ወራት የሚቆይ የ2012 የበጋ ወራት ተፋሰስ ልማት ሥራ ትናንት በይፋ ተጀምሯል፡፡ በክልሉ በሰው ሰራሽ ችግሮች ምክንያት የተፈጥሮ ሃብት በከፍተኛ ሁኔታ ከተጎዳባቸው አካባቢዎች አንዱ የአሶሳ ወረዳ ነው፡፡ በዘመቻው ከተሳተፉ የወረዳው አርሶ አደሮች መካከል አቶ አወልሙሄ ሃሰን እንደተናገሩት ከ2004 ጀምሮ ቤተሰባቸውን ጭምር በማስተባበር በዘመቻው እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡ ወይዘሮ ሂጂራ የሱፍ የተባሉ ነዋሪ በወረዳው በተከታታይ በተከናወኑ የተፋሰስ ልማት ሥራዎች  አካባቢው መልሶ ማገገም እንደጀመረ ይናገራሉ፡፡ “ጥቅሙን በሚገባ ተረድተን ስራውን ቀጥለናል” የሚሉት አርሶ አደሯ የደረቁ ምንጮች እየሞሉ በመምጣታው ለመስኖ የሚጠቀሙት ውሃ መጠን መጨመሩን አስረድተዋል፡፡ የተፋሰስ ልማት በተከናወነባቸው አከባቢዎች ዳግም የፈለቁ ምንጮችን ተጠቅሞ ወጣቱ በስፋት ወደ ሥራ እንዲገባ ለማድረግ መንግስት ድጋፉን እንዲያጠናክር ነዋሪዎቹ ጠይቀዋል፡፡ የእርሻ መሬት እንደሰው ይታመማል የሚሉት ደግሞ የክልሉ ግብርናና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ ተወካይ አቶ ፀሐይ አዳሙ ናቸው። ለመሬት መታመም ዋናው ምክንያት እኛው የሰው ልጆች ነን ያሉት አቶ ፀሀይ እየተከናወነ ያለው የተፋሰስ ልማት ደግሞ ዋነኛው የተፈጥሮ ሃብትን ማገገሚያ መንገድ መሆኑን  የተገኘውን ውጤት ዋቢ በመጥቀስ ገልፀዋል። “የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀማችን መጪውን ትውልድ ከግምት ውስጥ ያስገባ ሊሆን ይገባል” ሲሉም ተወካዩ መክረዋል፡፡ በተለይ የሃገር ኩራት የሆነውን የህዳሴው ግድብ ከደለል በማዳን ዘላቂ ልማትን ማምጣት ዋነኛው የተፋሰስ ልማት ስራው ዓላማ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ አመራሩ ህብረተሰቡን ከመደገፍ ጀምሮ ለውጤታማነቱ በቁርጠኝነት እንዲሰራም ተወካዩ አሳስበዋል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም