የጤና ባለሙያዎች የተከታታይ ሙያ ማጎልበቻ ስርዓት ተግባራዊነት በሚቀጥለው ዓመት ይጀምራል

85
አዲስ አበባ፣ ጥር 26/2012 ዓ.ም (ኢዜአ) የጤና ባለሙያዎች ወቅቱ የሚጠይቀውን እውቀትና ክህሎት እንዲይዙ የሚያስችል የተከታታይ ሙያ ማጎልበቻ ስርዓት በ2013 ዓ.ም መተግበር እንደሚጀምር የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ። ስርዓቱን ለመተግበር በዘርፉ ከተሰማሩ ማህበራትና ከክልሎች ጋር በትብብር እንደሚሰራም ሚኒስቴሩ ጠቁሟል። የሚኒስቴሩ የሰው ሃብት ልማት ዳይሬክተር አቶ አሰግድ ሳሙኤል ለኢዜአ እንዳሉት፤ ሚኒስቴሩ ብቃት ያለው የጤና ባለሙያ ዘርፉን እንዲቀላቀልና ታካሚውም በብቁ ባለሙያ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኝ እየሰራ ነው። የጤና ሙያ ጥራትን ለማሥጠበቅ ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር እና ከከፍተኛ ትምህርት ጥራትና አግባብነት ኤጀንሲ ጋር በመተባበር የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ ገልጸዋል። ይህን ተግባር አጠናክሮ ከመቀጠል ባለፈ የጤና ባለሙያዎች በሰለጠኑበት ሙያ የሚያስፈልገውን እውቀት፣ ክህሎትና አመለካከት መያዛቸውን ለመመዘን አገር አቀፍ ምዘና ተደርጎ ብቃታቸው ሲረጋገጥ ወደዘርፉ እየተሰማሩ መሆኑን ጠቅሰዋል። ሚኒስቴሩ በ2013 ዓ.ም መተግበር የሚጀምረው የተከታታይ ሙያ ማጎልበቻ ስርዓት ''የጤና ባለሙያዎች ወቅቱ የሚጠይቀውንና የቅርብ ጊዜ መድሃኒትና መመሪያዎችን ለማወቅ ይረዳቸዋል'' ብለዋል። ከዚህ ቀደም የጤና ባለሙያዎች ፈቃድ በየጊዜው ሲያድሱ የአገልግሎት ጊዜያቸው ብቻ ታይቶ ይታደስ እንደነበር አስታውሰው፤ ስርዓቱ ሲጀመር ባለሙያዎቹ ፈቃድ ሲያድሱ ከአገልግሎት ጊዜ በተጨማሪ ተከታታይ የሙያ ማጎልበቻ ስልጠና መውሰዳቸውን የሚያረጋግጥ መረጃ ማቅረብ እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል። ወቅቱ አዳዲስ የህክምና መሳሪያና መድሃኒቶች በወራት ውስጥ የሚለወጡበት በመሆኑ ባለሙያው በየጊዜው ራሱን እያበቃ መሄድ እንዳለበት አስገንዝበዋል። ስርዓቱን ከጤና ሙያ ማህበራት፣ ከክልሎችና ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በትብብር የሚተገበር መሆኑንም አቶ አሰግድ ገልፀዋል። ስርዓቱን ለመተግበር እውቅና የተሰጣቸው ተቋማት መለየታቸውን ሚኒስቴሩ አስታውቋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም