በፕሪሚየር ሊጉ በወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኘው ድሬዳዋ ከተማ እግር ኳስ ክለብ አሰልጣኙን አሰናበተ

73
አዲስ አበባ፣ ጥር26/2012 (ኢዜአ) በፕሪሚየር ሊጉ በወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኘው ድሬዳዋ ከተማ እግር ኳስ ክለብ የቡድኑን ዋና አሰልጣኝ ስምዖን አባይን አሰናበተ። ድሬዳዋ ከተማ ከባለፉት 12 የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ማግኘት ካለበት 36 ነጥብ ውስጥ 13 ነጥብ ብቻ በመሰብሰብ በፕሪሚየር ሊጉ ከሚጫወቱ 16 ክለቦች 15ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። በቡድኑ ውጤት ደስተኛ ያልሆነው የድሬዳዋ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ቦርድ ዋና አሰልጣኙን አሰናብቶ በምትካቸው በጊዜያዊነት ቡድኑን እንዲያሰለጥኑ አሰልጣኝ ፍሰሃ ፆመልሳንን መርጧል። በጊዜዊነት ቡድኑን እንዲመሩ የተሾሙት አሰልጣኝ ፍሰሃ በድሬዳዋ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ምክትል አሰልጣኝ ሆነው ሲሰሩ የነበሩ ናቸው። ድሬዳዋ ከተማ በ13ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በመጪው እሁድ ድሬዳዋ ላይ ከስሑል ሽረ ጋር ያለበት ጨዋታ በአዲሱ አሰልጣኝ የሚመራ ይሆናል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም