የኬንያው የቀድሞ ፕሬዚዳንት ዳንኤል አራፕ ሞይ በ95 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ

79
ጥር 26/2012 ዓ/ም (ኢዜአ) ኬንያን ከሁለት አስርት አመታት በላይ የመሩት የቀድሞ ፕሬዚዳንት ዳንኤል አራፕ ሞይ በ95 ዓመታቸው ትናንት ሌሊት ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ። ዳንኤል አራፕ ሞይ ኬንያን ለ24 ዓመታት በፕሬዚዳንትነት ያገለገሉ ሲሆን በተቃዋሚዎቻቸው እንደ አምባገነን መሪ ሲቆጠሩ በአንጻሩ በአጋሮቻቸው ደግሞ በምስራቅ አፍሪካ መረጋጋትን እንዳሰፈነ መሪ ተደርገው ይወሰዳሉ። የቀድሞው ፕሬዚዳንት በኬንያ ህገመንግስት ለተጨማሪ ጊዜ እንዳይወዳደሩ ከታገዱ በኋላ እ.አ.አ.በ2002 የስልጣን ዘመናቸው አብቅቷል። ከነፃነት በኋላ የኬንያ የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት የነበሩት ጆሞ ኬንያታ ህልፈተ ህይወት እ.አ.አ በ1978 ከተሰማ በኋላ ነው ዳንኤል አራፕ ሞይ ወደ ስልጣን የመጡት። በስልጣን ዘመናቸው በሚዛናዊነት የሚፈሩና የሚደነቁ መሪ እንደነበሩ በርካቶች የሚናገሩላቸው ዳንኤል አራፕ ሞይ አምባገነን መሪ እንደነበሩ የሚገልጹና የሚወቅሷቸውም ነበሩ። በ1991 ለአገሪቱ የብዝሀ ፓርቲ ስርዓትን ቢያስተዋውቁም ከዚያ በኋላ የተደረጉ ምርጫዎች ሙሉ በሙሉ ተሰርዘዋል። ከኬንያው የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት ጆሞ ኬንያታ በበለጠ የህዝብ ተቀባይነት ያገኙ ፖለቲከኛ የነበሩት ዳንኤል አራፕ ሞይ በሙስና ክስና ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ድቀት እንደ ዋነኛ ተጠያቂ ተደርገው ይወሰዳሉ። እ.ኤ.አ. መስከረም 2 ቀን 1924 ከአርሶ አደር ቤተሰብ የተወለዱት ዳንኤል አራፕ ሞይ በ1963 ኬንያ ነፃነቷን እንድታገኝ በተደረገ ትግል የጆሞ ኬንያታ የቅርብ ወዳጅ ነበሩ። ቢቢሲ እንደዘገበው ዳንኤል አራፕ ሞይ ከ1964 እሰከ 1967 የውስጥ ጉዳዮች ሚኒስትር ሆነው ያገለገሉ ሲሆን በ1967 ደግሞ የአገሪቱ ምክትል ፕሬዚዳንት ለመሆን በቅተዋል። በፕሬዚዳንት ዘመናቸው በመንግስት የብዙሃን መገናኛ በመታገዝ በሁሉም የኑሮ ጉዳዮች ላይ የበላይነት ለማምጣት ጣልቃ ይገቡ እንደነበርም ይነገርላቸዋል። ተቃዋሚዎቻቸው የእርሳቸውን የስልጣን ዘመን እንደ የጥፋት ዓመታት የሚመለከቱት ሲሆን ኬንያ በሙስና፣ በጎሳ ግጭቶች እና በሰብአዊ መብት ጥሰቶች ስሟ እንዲነሳ ያደረጉ መሪ ናቸው በሚልም ይከሷቸዋል። ከእርሳቸው በተቃራኒ መስመር የቆሙ ሰዎችን ለመቅጣት የመንግስት ሀብቶችን በመጠቀም ለታማኝ አገልጋዮቻቸው ሽልማት ይሰጡ እንደነበር የሚነገርላቸው ዳንኤል አራፕ ሞይ “መንግስትን ልክ እንደ ግል እርስታቸው ይመለከታሉ” ሲሉ ተቃዋሚዎቻቸው ይተቿቸዋል። ይሁን እንጂ የኬንያው ቀድሞ ፕሬዚዳንት ዳንኤል አራፕ ሞይ ደጋፊዎች በርካታ የአፍሪካ አገሮች በሰላም እጦት ውስጥ በነበሩበት ጊዜ ኬንያ “ሰላማዊ” እንደትሆን አድርገዋል በሚል ይከላከሉላቸዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም