ሴቶችና ህጻናት የግጭት መሳሪያ እንዳይሆኑ የተጠናከረ ጥበቃ መደረግ አለበት

84

አዲስ አበባ  ጥር (ኢዜአ) 26/2012 የሴቶች ማህበራት ቅንጅት ሴቶችና ህጻናት የግጭት መሳሪያ እንዳይሆኑ የተጠናከረ ጥበቃ መደረግ እንዳለበት አስገነዘበ።

በኢትዮጵያ ሴቶችና ህጻናት የግጭት ሰለባ እንዳይሆኑ እየተደረገ ያለው ጥበቃ ይበልጥ መጠናከር እንዳለበትም አስገንዝቧል።

ከደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ አቅራቢያ ታግተው የተወሰዱ ተማሪዎች ሁኔታ ሴቶች የግጭት ሰለባ እንዳይሆኑ መጠንቀቅ እንደሚያስፈልግ የሚያሳይ 'የማስጠንቀቂያ ደወል' ሊሆን እንደሚገባም ገልጿል።

የሴቶች ማህበራት ቅንጅት ዋና ዳሬክተር ወይዘሮ ሳባ ገብረመድህን ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ አፍሪካን ጨምሮ በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ሴቶችና ህጻናትን ለጦርነትና ግጭት መሳሪያነት ማዋል በኢትዮጵያ እንዳይለመድ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል።

ዋና ዳሬክተሯ "ወጣት ሴቶች መታገታቸውና እስካሁን ያሉበት አለመታወቁ ለሁሉም ሴቶች ስጋትን የሚፈጥር ነገር ነው" ሲሉ ገልጸዋል።

በመሆኑም መንግስት መሰል ክስተቶች እንዳያጋጥሙ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል።

በዚህም ለሴቶች የሚደረገውን ጥበቃ ማጠናከር እንደሚኖርበት የተናገሩት ወይዘሮ ሳባ፤ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለመከላከል የሁሉንም አካላት ጥረት እንደሚጠይቅ አስታውቀዋል።

መንግስት የሚያወጣቸው መረጃዎች ህዝብን ግራ እንዳያጋቡና እምነት እንዳያሳጡ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት አመልክተዋል።

በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሴቶች በትምህርትና በአመራር ያላቸው ተሳትፎ እየተሻሻለ ባለበት ወቅት በተማሪዎቹ ላይ የተፈጸመው እገታ  "በእንጭጩ" ሊገታ የሚገባው ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሲቪል ማህበራት፣ የአገር ሽማግሌዎች እንዲሁም ኅብረተሰቡ ሴቶች የግጭት መሳሪያ እንዳይሆኑ ድርሻውን እንዲወጣ ዋና ዳይሬክተሯ ጠይቀዋል።

''አጥፊዎችን በመታገል ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት እንደ ናይጀሪያ ባሉ የአፍሪካ አገሮች የተከሰቱት ተመሳሳይ ድርጊቶች እንዳይደገሙ ማድረግ ይገባል'' ብለዋል።

በኢትዮጵያ በሴቶች ላይ ያለእድሜ ጋብቻ፣ ግርዛት፣ መደፈርና ሌሎች የሚፈጸሙ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ቢዘወተሩም፤ ሴቶችን ማገት ግን እንግዳ ክስተት እንደሆነ ገልጸዋል።

የእርስ በርስ ግጭት የበረታባት የአፍሪካ አህጉር የሴቶች ጾታዊ ጥቃት፣ ሞት፣ አካላዊ ጉዳት እየጨመረ መምጣቱን መረጃዎች ያሳያሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም