በወልዲያ ከተማ ለወጣቶች የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ተሰጠ

60
ወልዲያ ፣ጥር 26/2012 (ኢዜአ) በወልዲያ ከተማ አስተዳደር ለ333 ወጣቶች የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ መስጠቱን የከተማ አስተዳደሩ ገለጸ። ለወጣቶቹ  የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ የረጅም ጊዜ ጥያቄ ሆኖ በመቆየቱ አሁን ላይ ይህን ጥያቄ ለመመለስ መሰጠቱን የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አቶ ደንበሩ ተስፋው የቦታው ርክክብ በተካሄደበት ወቅት ተናግረዋል። ቦታው የተሰጠው ከወልዲያ ዙሪያ ወረዳ ወደ ከተማ አስተዳደሩ በተካተቱ አራት ቀበሌዎች ይኖሩ ለነበሩ የአርሶ አደር ልጆች ነው። ቦታውም የመንግስት ሰራተኛ ላልሆኑ፣ ከዚህ በፊት በውርስም ይሁን በምሪት ቦታ ላላገኙና አነስተኛ ገቢ ላላቸው ወጣቶች የተላለፈ መሆኑን ምክትል ከንቲባው አስረድተዋል። ወጣቶቹ በተሰጣቸው ቦታ ላይ አቅማቸውን የሚመጥን ቤት በመስራት ሊገለገሉበት እንደሚገባና ለመሸጥም ሆነ ወደ ሌላ አካል ከማዛወር እንዲቆጠቡ አሳስበዋል። በቅርቡም ጀነቶ በር በተባለው ቀበሌ ለሚኖሩ 500 ወጣቶች በተመሳሳይ ለመስጠት ቦታ መዘጋጀቱን ጠቅሰው በቀሪዎቹ ሁለት የገጠር ቀበሌዎችም እንዲሁ እንደሚቀጥል ገልጸዋል። እየተሰጡ ላሉ ቦታዎችም በቅርቡ የመሰረተ ልማት ግንባታ እንደሚሟላላቸውም  አስታውቀዋል። በወልዲያ ከተማ የወጣት ማህበር አማካሪ ወጣት አለበል ደምሴ  የወጣቶች የቤት መስሪያ ቦታ ጥያቄ ለረጅም ጊዜ ሲነሳ የነበረና የመልካም አስተዳደር ችግር ሆኖ መቆየቱን ተናግሯል። አሁን ላይ  የወጣቶችን ጥያቄ መመለስ መጀመሩ መልካም መሆኑን ገልጾ "ቀጣይ የእድሉ ተጠቃሚ ያልሆኑ ወጣቶች ችግራቸው እንዲፈታም ከከተማ አስተዳደሩ ጋር እንሰራለን "ብሏል። ወጣት አዲሱ አዳነ በበኩሉ የቤት መስሪያ ቦታ እንዲሰጣቸው ሲያቀርቡት የቆየው ጥያቄ አሁን ምላሽ በማግኘቱ መደሰቱን ገልጿል። ወጣቶቹ በተሰጣቸው የመስሪያ ቦታ በ21 ማህበራት በመደራጀት የሚገነቡ ሲሆን  ለእያንዳንዳቸው የሚደርሳቸውን ይዞታም ተረክበዋል። በቦታ ርክክቡ ስነ ስርዓት ወቅት የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች፣ ወጣቶችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።              
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም