በደሴ ከተማ አንድ ሺህ የጎዳና ተዳዳሪዎችን ከጎዳና የማንሳት ስራ ተጀመረ

73
ደሴ፣ ጥር 26/2012 ዓ.ም (አዜአ) በደሴ ከተማ አስተዳደር በከተሞች ምግብ ዋስትና እና ሥራ እድል ፈጠራ ፕሮግራም አንድ ሺህ የጎዳና ተዳዳሪዎችን ከጎዳና የማንሳት ስራ መጀመሩን የከተማው ምክትል ከንቲባ አስታወቁ። ምክትል ከንቲባው አቶ መላኩ ሚካኤል ትናንት ፕሮግራሙ ሲጀመር እንደገለጹት በኢትዮጵያ በ11 ከተሞች በምግብ ዋስትናና ስራ እድል ፈጠራ ከታቀፉ ከተሞች ውስጥ ደሴ ከተማ አንዷ ናት፡፡ በዚህም ከ18 ሺህ በላይ በዝቅተኛ ኑሮ ደረጃ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ተለይተዉ በተለያዩ የከተማ ልማት ስራዎች በማሳተፍ ኑሮአቸውን እንዲያሻሻሉ እየተደረገ ነው። የዚሁ ፕሮግራም አካል የሆነው የጎዳና ተዳዳሪዎችን ከጎዳና የማንሳትና የማብቃት የሶስት ዓመት እቅድ በጥናት የተለዩ አንድ ሺህ ጎዳና ተዳዳሪዎችን ከጎዳና በማንሳት በኢኮኖሚ እራሳቸውን የማስቻል እንቅስቃሴ ተጀምሯል ። በመጀመሪያዉ ዙር ከ18 ዓመት በታች ዕድሜ ያላቸው 300  ታዳጊዎችን ከጎዳና ኑሮ በማላቀቅ ለዚሁ በተዘጋጀ ማዕከል በማስገባት የተለያዩ ስልጠናዎች እንዲያገኙ የሚደረግ ሲሆን ቀሪዎች 700 የጎዳና ላይ ተዳዳሪዎችም ደግሞ በቀጣይ ሁለት ዓመታት ከጎዳና ህይወት እንዲላቀቁ ይደረጋል። የከተማ አስተዳደሩም ፐሮግራሙ ውጤታማ እንዲሆን በማገዝና የሥራ እድል እንዲፈጠርላቸው በማድረግ የበኩሉን ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን ከንቲባው ተናግረዋል። የደሴ ከተማ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ መዓዛ ሃይለጊዮርጊስ በበኩላቸው በመጀመሪያው ዙር 300 ታዳጊዎችን ከጎዳና አንስተዉ እንዲያገግሙ የሚደርጉ ሁለት ማእከላት ተከፍተዋል። ከጎዳና ህይወት የሚነሱት ታዳጊ ወጣቶች በማእከላቱ መሰረታዊ ፍላጎታቸው  ተሟልቶላቸው ከ6 ወር እስከ 3 ዓመት እንዲቆዩ በማድረግ የሱስ ተጠቂዎችን እንዲያገግሙ የምክር አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ጠቅሰዋል። ከማዕከላቱ አገግመው የሚወጡት የስራ እድል እንዲፈጠርላቸው እንደሚደረግ ጠቅሰው ከቤተሰቦቻቸው ለመቀላቀል ፍላጎት ያላቸውም ሁኔታዎች ይመቻችላቸዋል ብለዋል። አዲስ ጎዳና ተዳዳሪዎች እንዳይተኩም ከባለድርሻ አካላት የተወጣጣ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል። ጎዳና ተዳዳሪዎችን በማዕከል  ለማብቃት ከፌደራል መንግስት ጋር ውል ተፈራርሞ የገባው "አሳድ" የተባለው ድርጅት የደሴ ቅርንጫፍ ማስተባበሪያ ኃላፊ አቶ አወል መሃመድ በበኩላቸው እድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሚገኙ ታዳጊዎችን በመንከባከብና እዲያገግሙ ለማድረግ ወደ ስራ መግባቱን አስረድተዋል። የከተሞች ምግብ ዋስትናና ሥራ አድል ፈጠራ ፕሮግራም በደሴ ከተማ ከተጀመረ 3ኛ ዓመቱ መያዙ ታውቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም