በደምቢ ዶሎ ስለታገቱ ተማሪዎች ኃላፊነት የሚወስድ አካል ያለመገኘቱ ጉዳዩን ውስብስብ አደርጎታል - መንግስት

89
አዲስ አበባ ጥር 25/2012 (ኢዜአ) የደምቢ ዶሎ ተማሪዎችን እገታ ፈጽሜያለው ብሎ ኃላፊነቱን የሚወስድ አካል ያለመገኘቱ ጉዳዩን ውስብስብ እንዳደረገው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተናገሩ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እየተካሄደ ባለው ልዩ ስብሰባ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ጥያቄዎች ምላሽ እየሰጡ ነው። ከሁለት ወራት በፊት ለታገቱ የደምቢ ዶሎ ተማሪዎች መንግስት እየወሰደ ያለውን እርምጃ በተመለከተ ተጠይቀው በሰጡት ማብራሪያ እገታውን ፈጸምኩ የሚል አንድም አካል ወይም ቡድን አለመገኘቱ ጉዳዩን ወሰብስብ እንዳደረገው ገልጸዋል። ''አጋቹ ኃይል እኔ ነኝ" ብሎ ሃላፊነቱን የወሰደ ባለመኖሩ በጉዳዩ ላይ እንዳሻን መናገር እንዳችል፤ እንዳሻን በመናገራችንም የሰው ሕይወት አደጋ ውስጥ እንዳይገባ ጥንቃቄ ያስፈልጋል ነው ያሉት። በተደረሰባቸው መረጃዎች መሰረት እገታው ደርሶባቸዋል ከተባሉት ግለሰቦች መካከል ተማሪዎች ያልሆኑና በተባለው ስፍራም ነዋሪ ያልሆኑ ታጋቾች እንደተገኙ አንስተዋል። መከላከያ በስፍራው በሚያደርገው ኦፕሬሽን እስካሁን ድረስ በአንድም ስፍራ የተጎዳ ወይም የሞተ ሰው እንደሌለም ገልጸዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ። ''መንግስት ለምንድነው የደረሰበትን መረጃ በወቅቱ የማይገልጸው? የሚል ተግሳጽ ይነሳል'' ያሉት ዶክተር አብይ ባልተሟላ መረጃ ጠንከር ያለ መግለጫ በሚሰጥበት ወቅት ያልተደራጁ ግለሰቦች ያደረጉት እገታ ከሆነ ራሳቸውን ለማዳን ሲሉ ታጋቾቹን አደጋ ውስጥ ሊከቱ እንደሚችሉ ነው የተናገሩት። በመሆኑም የመንግስት ፍላጎት ምንም ሰው ሳይሞት በሕይወት እንዲገኙ ስለሆነ ከመናገር ይልቅ በሕይወት የማስገኘቱ ጉዳይ ቅድሚያ የተሰጠው ስራ እንደሆነም አስረድተዋል። እስካሁን በተደረገው አሰሳ በሁሉም ቀበሌዎችና ወረዳዎች ተጎድቶ የተገኘ ሰው የለም ብለዋል። በጉዳዩ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የሠላም ሚኒስትርና ከፍተኛ የጸጥታ ኃላፊዎች በኮሚቴ እየሰሩ መሆኑንና የደረሱበትንም ስራቸውን በሚያጠናቅቁበት ወቅት ለሕዝብ እንደሚያሳውቁ ገልጸዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም