የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ከቻይና ኩባንያዎች ጋር በኢትዮዽያ በሚገኙ የኢንቨስትመንት አማራጮች ዙሪያ ውይይት አካሄደ

66
አዲስ አበባ ሰኔ 19/2010 የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ከቻይና ኩባንያዎች ተወጣጥቶ ወደ ኢትዮጵያ ከመጣ የልዑካን ቡድን ጋር በኢትዮዽያ ስላሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች ውይይት አካሄደ። በውውይቱ ሁናን ከተሰኘው የቻይና ግዛት ከ80 በላይ የኮንስትራክሽን ኩባንያዎች የተወጣጣ የልዑካን ቡድን አባላት ተሳታፊ ሆነዋል። የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት  ዳይሬክተር ጄኔራል ኢንጂነር ሞገስ ጥበቡ ከግብርና ቀጥሎ ለኢትዮጵያውያን ሰፊ የስራ እድል በሚፈጥረው የኮንስትራክሽን ዘርፍ መሰማራት አዋጭ መሆኑን ለልዑካን ቡድኑ ገልጸዋል። በቻይና የኮንስትራክሽን ዘርፍ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በቤቶች ግንባታና በማዕድን ዘርፍ ልማት ቢሰማሩ ትርፋማ እንደሚሆኑም አስታውቀዋል። ኩባንያዎቹ በኤርፖርቶች ማስፋፊያ ፕሮጀክት በተለያዩ የግድብ ግንባታዎች እንዲሁም በመንገድና በባቡር መስመር ግንባታ ዘርፍም መሰማራት የሚችሉበት አማራጭ እንዳለ ተገልጾላቸዋል። የኮንስትራክሽን ሚኒስትር ኢንጅነር አይሻ መሀመድ በበኩላቸው ''የኢትዮጵያ መልክዓ ምድር አቀማመጥ ለገበያ ትስስር አመቺና ለመካከለኛው ምስራቅም ቅርብ መሆኑ አገሪቱን ለኢንቨስተሮች ተመራጭ አድርጓታል'' ብለዋል። የቴክኖሎጂ አለመሟላትና የግንባታ መጓተት ችግር ላለባት ኢትዮጵያ በኮንስትራክሽን ዘርፍ በዓለም ላይ ትልቅ ስምና እውቅና ያላቸው የቻይና ሁናን ግዛት ኩባንያዎች በዘርፉ እንዲሰማሩ የአገሪቱ ፍላጎት እንደሆነ ሚኒስትሯ ተናግረዋል። የግንባታ ፕሮጀክቶችን በጊዜው ሰርቶ የማጠናቀቅ ሰፊ ተሞክሮ ያላቸው የሁናን ግዛት ኩባንያዎች በኢትዮዽያ ኢንቨስት ማድረጋቸው አገሪቱን በሚያዋስኗት ኬንያ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያ፣ ጂቡቲና ኤርትራ የገበያ አማራጭ በመፍጠር በአገሮቹ በዘርፉ እንዲሰማሩ እድል እንደሚፈጥርላቸውም አብራርተዋል። የሁናን ግዛት አስተዳዳሪ ሚስተር ሹ ዳዝህ በግዛቷ የሚገኙ ኩባንያዎች ችግርን ተቋቁመው ለስኬት የሚበቁ በርካታ መሀንዲሶች ያሏቸውና በረጅም ጊዜ ልምድ የተቃኙ በመሆናቸው በኢትዮጵያም ውጤት እንደሚያስመዘግቡ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል። በኢትዮጵያ በፈጣን እድገት ላይ በሚገኘው የግንባታ ዘርፍ የቻይና ኩባንያዎች ቢሳተፉ ለውጡን የበለጠ ውጤታማ እንደሚያደርጉት ለማሳየት የውይይቱ ተሳታፊ ኩባንያዎች ከዚህ በፊት በተለያዩ አገሮች በኩባንያዎቹ የተሰሩ ግዙፍ የግንባታ ውጤቶችን አቅርበዋል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ዮናስ አያሌው በቻይና በኮንስትራክሸን ዘርፍ  ተሰማርተው የሚገኙ ኩባንያዎች በመዲናዋ በቤቶች ግንባታ ዘርፍ ቢሰማሩ ሰፊ አማራጭ እንዳለ ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም