የቆላ ስንዴ መስኖ ልማት ፕሮጀክቱን እውን ለማድረግ መንግስት ከአርሶ አደሩ አቅም በላይ የሆኑ ግብዓቶችን ማቅረብ አለበት

157
አዲስ አበባ፣ጥር 24/2012 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የተጀመረውን የቆላ ስንዴ መስኖ ልማት ፕሮጀክት እውን ለማድረግ መንግስት ከአርሶ አደሩ አቅም በላይ የሆኑ ግብዓቶችን ማቅረብ እንደሚጠበቅበት አምራቾች ገለጹ። የኢትዮጵያ የስንዴ ፍላጎት በየጊዜው እያደገ በመምጣቱ ከውጭ አገር ገቢ የሚደረገው የስንዴ ምርት ከ25 በመቶ ወደ 30 በመቶ ከፍ ብሏል። በዚህም በአገር ውስጥ ከሚመረተው 48 ሚሊዮን ኩንታል በተጨማሪ 1 ነጥብ 7 ሜትሪክ ቶን ስንዴ ከውጭ እንድታስገባ ትገደዳለች። በዚህም ከውጭ የሚገባውን የስንዴ ምርት በአገር ውስጥ ለመሸፈን መንግስት በአዋሽ፣ ዋቢ ሸበሌና ኦሞ ወንዝ ተፋሰሶች ላይ የቆላ ስንዴ መስኖ መርሃ ግብር የሙከራ ስራ ጀምሯል። በ2012 ዓ.ም የበጋ መስኖ ወቅት በሶስቱ ተፋሰሶች 15 ሺህ 100 ሄክታር መሬት የቆላ ስንዴ በተለያዩ አምራቾች መሸፈን ችሏል። መንግስት የጀመረው አገራዊ የቆላ ስንዴ መስኖ መርሃ ግብር ግቡን እንዲመታ በቂ የግብርና ግብዓት ማቅረብ እንዳለበት አምራቾች ይስማማሉ። በአፋር ክልል አሚባራ ወረዳ የዲስሪ ቀበሌ አርሶ አደር የሆነችው ወጣት ዘምዘም ሲራጅ በ 12 ሄክታር መሬት ላይ ስንዴ ታለማለች። "እኔ አርሶ አደር እንጂ ኢንቨስተር አይደለሁም" የምትለው ወጣት ዘምዘም፤ ''በአርሶና ከፊል አርብቶ አደር አቅም መግዛት የማይቻለውን ትራክተር በኪራይም ቢሆን በወቅቱ ሊቀርብልን ይገባል'' ብለዋል። በአንድ አካባቢ አንድ ወይም የተወሰኑ ግለሰቦች ብቻ ስንዴ እያመረቱ አካባቢው ሜዳ ሲሆን ከቡቃያው ጀምሮ ሰብሉ ለጉዳት ይጋለጣል። ''ማኅበረሰቡ ለስንዴ ማምረት አዲስ ቢሆንም ጥቅሙን ተረድቶ ወደ ስራ እንዲገባ መንግስት ማነሳሳት ይኖርበታል፤ እኛም እናግዛለን'' ብለዋል። ከስንዴ ምርት የሚገኘው ጥቅም ከሌሎች ሰብሎች የተሻለ መሆኑን የሚናገሩት አምራቾቹ፤ ይሄንን አይተው ሌሎችም እየተቀላቀሉ እንደሆነ ተናግረዋል። ''ሁልጊዜ ድጋፍ ባንፈልግም ለስራው አዲስ በመሆናችን በራሳችን አቅም መስራት እንስከምንችል እገዛ ሊያደርግልን ይገባል'' ይላሉ። የመልካ ወረር እርሻ ልማት ለትርፍ የተቋቋመ ድርጅት መሆኑን የገለጹት ስራ አስኪያጁ አቶ ሃይማኖት፤ ''ማኅበረሰቡን በማገዝ ለአገራዊው እቅድ መሳካት የበኩላችንን አስተዋጽኦ እናበረክታለን'' ብለዋል። ከውጭ የሚገባውን የስንዴ ምርት በአገር ውስጥ ምርት ለመሸፈን በመንግስት እቅድ ተይዞ እየተተገበረ ይገኛል። የውሀ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ የግብርና ሚኒስቴር እና የገንዘብ ሚኒስቴር አባል የሆኑበት ኮሚቴ ተዋቅሮ ስራውን እየተከታተለ እንደሚገኝም ይታወቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም