ቁጥራቸው ከ800 በታች የሆኑትን የሳይካትሪ ባለሙያዎች ጥምርታ ለማጣጣም እየተሰራ ነው

89
አዲስ አበባ (ኢዜአ ) ጥር 24/2012 በኢትዮጵያ ቁጥራቸው ከ800 በታች የሆኑትን የስነ-አዕምሮ (ሳይካትሪ) ባለሙያዎች ጥምርታ ከህዝብ ቁጥር ጋር ለማጣጣም እየሰራ እንደሚገኝ ጤና ሚኒስቴር ገለጸ። ሚኒስቴሩ ከሶስት አመት በፊት የስፔሻላይዝድ ወይም በአንድ ዘርፍ ላይ አተኩረው የሚሰሩ ባለሙያዎችን ቁጥር ለማሳደግ እየተገበረው ባለው መርሃግብር ላይ ከ70 በላይ ሀኪሞች የሳይካትሪ ስፔሻሊቲ ስልጠና እየወሰዱ እንዳሉ ገልጿል። የሚኒስቴሩ የሰው ሃብት ልማት ዳይሬክተር አቶ አሰግድ ሳሙኤል ለኢዜአ እንዳሉት፤ በጤናው ዘርፍ የሰው ኃይልን በሚፈለገው ደረጃ ለማፍራት እየተሰራ ሲሆን በዚህም የጤና ባለሙያዎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል። እየጨመረ የመጣውን ተላላፊ ያልሆኑ በሸታዎችን ስርጭት ለመቀነስ የአዕምሮ ጤና ህክምናን ጨምሮ ለሌሎች ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በቂ ትኩረት በመስጠት እየተሰራ እንደሚገኝም አመልክተዋል። የአዕምሮ ጤና ችግርን ለማከም የሚችሉ በተለያየ ደረጃ የሚገኙ 753 ባለሙያዎች በክልልና ፌዴራል ጤና ተቋማት አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙም ተናግረዋል። የባለሙያዎቹን ቁጥር ለማሳደግና ጥምርታውን ካለው ህዝብ ጋር ለማቀራረብ ስምንት የመንግስት የትምህርት ተቋማት የስነአዕምሮ ትምህርት ስልጠና እየሰጡ መሆናቸውን ጠቁመዋል። ከሶስት አመት በፊት የስፔሻሊቲን ቁጥር ለማሳደግ በማለም በተጀመረው መርሃግብር ከ78 በላይ ሀኪሞች በሳይካትሪ ስፔሻሊቲ ስልጠና ላይ እንደሚገኙም ተናግረዋል። በአገሪቱ በሳይካትሪ ዘርፍ ያሉ ባለሙያዎች ከህዝቡ ቁጥር አንፃር ያላቸው ጥመርታ ሲታይ አነስተኛ መሆኑንም ነው አቶ አሰግድ ያስረዱት። ከሳይካትሪ በተጨማሪ በሌሎች የህክምና ዘርፎችም በቂ ባለሙያ ለማፍራት ሚኒስቴሩ በስፋት እንደሚሰራም ገልጸዋል። በጤና ተቋማት የሚሰጡ የህክምና አገልግሎቶች በእድሜ የተከፋፈሉ መሆናቸውን አንስተው፤ ''በስነ-አዕምሮ ዘርፍም ፔዲያትሪክ ተብሎ ለህፃናት በተለዩ ክፍሎች መሰል ህመም ያለባቸው ህፃናት አገልግሎቱን እያገኙ ነው'' ብለዋል። የዘርፉ ባለሙያዎች አጠቃላይ ስልጠና ወስደው ስለሚመጡ አዋቂ፣ ህፃናትም ሆኑ በእድሜ የገፉ ሰዎችን ማገልገል የሚያስችል ክህሎትና እውቀት ያላቸው  ብለዋል። ባለሙያዎች በምን ዘርፍ ላይ አተኩረወ መስራት ስፔሻላይዝ ማደረግ እንዳለባቸው እንዲሁም ሌሎች የጤናው ዘርፍን ያማከሉ ስራዎችን የሚያመላክት ጥናት እየተደረገ በመሆኑ በጥናቱ ውጤት መሰረት በሳይካትሪ ዘርፍ በትኩረት የሚሰራበት ዘርፍ መሆኑን ጠቁመዋል። በዚህም መሰረት በሳይካትሪም ሆነ በሌላው ዘርፍ የጥናቱን ውጤት ከባለሙያና ተገልጋይ አስተያየት ጋር በማድረግ የሰው ኃይል ልማት ላይ ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የሙያ ስልጠናዎች እንደሚሰጡ አስረድተዋል። የጥናቱ ውጤት በሁለተኛው የጤናው ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን እቅድ የሚካተት መሆኑን ጠቁመው ጥናቱ የሚያመላክታቸው ሃሳቦች በየጊዜው እየተተገበሩ እንደሚሄዱ አቶ አሰግድ ገልፀዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም