ከቻይና ውጪ በኮሮና ቫይረስ የሰው ህይወት አለፈ

41
ጥር 24/2012 (ኢዜአ) በፊሊፒንስ ከቻይና ውጪ ለመጀመሪያ ጊዜ በኮሮና ቫይረስ የአንድ ሰው ህይወት አለፈ። በቫይረሱ ህይወታቸው ያለፈው የ44 ዓመቱ ቻይናዊ ኮሮና ቫይረስ ለመጀመሪያ ጊዜ በተቀሰቀሰበት የሁቤይ ግዛት መዲና በሆነችው ዉሃን ከተማ ለረጅም ጊዜ ነዋሪ እንደነበሩ ተጠቅሷል። ህይወቱ ያለፈው ቻይናዊው  ግለሰብ በውሀን ግዛት በበሽታው ተይዞ ወደ ፊሊፒንስ መግባቱንም የአለምጤና ድርጅት አስረድቷል፡፡ ግለሰቡ በቫይረሱ መያዛቸው እንደታወቀ ከአንድ ሌላ በቫይረሱ የተያዘች እንስት ጋር ለብቻቸው በማቆያ ስፍራ ሆነው ህክምናውን ተከታትለው  ተሽሎአቸውም ነበር ። ይሁንና ባለፉት 24 ሠዓታት ውስጥ ግለሰቡ በሽታው እንደጸናባቸው ጠቅሰው በመጨረሻም ለህልፈት መዳረጋቸውን ኒዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ዘግቧል። ፊሊፒንስ በኮሮና ቫይረስ አንድ ሰው ከሞተባት በኋላ ወደ ቻይና እንዲሁም ከቻይና ወደ ፊሊፒንስ የምታደርገውን የአውሮፕላን ጉዞ ሙሉ በሙሉ ሰርዛለች። አሜሪካና አውስትራሊያም በጊዜያዊነት ወደ ቻይናና ከቻይና ወደ አገራቸው የሚያደርጉትን የአውሮፕላን በረራ አቁመውታል። ቬትናምና ጃፓንም ተመሳሳይ ውሳኔ አሳልፈዋል። በበሽታው ከ300 በላይ ሰዎች ህይወታቸው ሲያልፍ ከ14 ሺህ  በላይ ደግሞ በበሽታው ተይዘዋል፡፡ በተመሳሳይ የ11 ሚሊዮን ነዋሪ ያላት ዉሃን ከተማ እስከ አሁን 31 ሰዎች ሞተውባታል። ይህንንም ተከትሎ በርካታ አገሮች ዜጎቻቸውን ከቻይና የማስወጣት ሂደት ላይ ናቸው። ለአብነትም ሳውዲ አረቢያ 10 ተማሪዎቿን ከዉሃን ከተማ እንዲወጡ አድርጋለች። ደቡብ ኮሪያ፣ ህንድና ባንግላዲሽም በተመሳሳይ ዜጎቻቸውን እያስወጡ ነው። ኢንዶኔዥያና ቱርክም ዜጎቻቸውን ከቻይና ለማስወጣት የራሳቸውን አውሮፕላን ወደ ቻይና መላካቸው ተገልጿል። በነገው ዕለት ደግሞ ራሺያ ዜጎቿን ለማስወጣት የጦር አውሮፓላኗን ወደ ቻይና ትልካለች ተብሏል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም