የጥላቻ ንግግርን በዘላቂነት ለመግታት በችግሩ ምንጭ ላይ መስራት ይገባል

78
አዲስ አበባ  ጥር 23/2012 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እየተበራከተ የመጣው የጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃ በዜጎች ደህንነት ላይ ስጋት ደቅኗል። በቅርቡም በአንዳንድ አካባቢዎች የዜጎች መፈናቀል፣ የንብረት ውድመት፣ ባስ ሲልም የሰው ሕይወት እስከመጥፋት ያደረሰ አደጋ ሲከሰት ተስተውሏል። እንደ አውሮጳዊያኑ አቆጣጠር 1994 በሩዋንዳ፤ በ20ኛ ክፍለ ዘመን አጋማሽ በጀርመንና በአውሮጳ የደረሰው አሰቃቂ የዜጎች እልቂት የጥላቻ ንግግር በጊዜ ካልተገታ የሚያመጣው ጥፋት ከባድ መሆኑን አመላካች ነው። ይህን አይነቱ ችግር በኢትዮጵያ እንዳይከሰት ለመከላከል መንግሥት የጥላቻ ንግግርና የሀሰተኛ መረጃ አዋጅ ለማፅደቅ በሂደት ላይ ይገኛል። ረቂቅ አዋጁ ዜጎች ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብታቸውን ሲጠቀሙ ግጭት ወይም ሁከት የሚቀሰቅስ፣ ብሄር፣ ኃይማኖት፣ ዘር፣ ጾታ፣ አካል ጉዳተኝነት፣ ግለሰብ ወይንም ቡድኖች ላይ ጥላቻ የሚያስነሱ ንግግሮችን መጠቀምን ይከለክላል። የተቀመጠውን ክልከላ ተላልፈው የተገኙ ዜጎች እንደ ጥፋቱ ደረጃ ከአንድ እስከ አምስት ዓመት እስር ሊፈረድባቸው፤ ከ50 ሺህ እስከ 100 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት ሊጣልባቸው እንደሚችልም ይደነግጋል። የፎርቹን ጋዜጣ ማኔጂንግ ኤዲተር አቶ ታምራት ገብረጊዮርጊስ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ አዋጁ ከዚህ ቀደም እንደነበረው የጸረ-ሽብር አዋጅ የዜጎችን የመናገር ነጻነት እንዳይገድብ ስጋታቸውን ገልጸዋል። የጥላቻ ንግግርን በሕግ ብቻ ማስቆም እንደማይቻል የገለጹት አቶ ታምራት ችግሩን በዘላቂነት ለማስወገድ የጥላቻ ምንጭ የሆኑ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ሳንካዎችን ማንሳት የተሻለ ነው ሲሉ ይሞግታሉ። ዜጎች የሚደርስባቸው ግፍ፣ መገለል፣ በእኩል አለመታየትና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ለጥላቻ መንስኤ ሊሆኑ እንደሚችሉ ጠቅሰው በዚህ ሳቢያ ለመጣ የጥላቻ ንግግር ቅጣት ብቻ መፍትሄ አይሆንም ባይ ናቸው። ''የጥላቻ ንግግር ሕግ የደነገጉ ታላላቅ አገራት ጭምር የሚፈልጉትን ውጤት አለማግኘታቸው በጥናት ተረጋግጧል'' ነው ያሉት አቶ ታምራት። እንደ አቶ ታምራት ገለጻ ሕግ አውጪዎች በ'አደገኛ ንግግር' እና 'አስቀያሚ ንግግር' መካከል ያለውን ልዩነት በአግባቡ መለየት አለባቸው። ንግግር አድራጊው ያለው ቦታ፣ የተናገረበት ሁኔታና ሌሎች ጉዳዮችን ከግምት ማስገባት እንደሚገባም ያብራራሉ። የሰብዓዊ መብት ኮሚሽነሩ ዶክተር ዳንኤል በቀለ በበኩላቸው በማኅበራዊ ሚዲያውና በሌሎች መገናኛ መስኮች እየተሰራጨ ያሉ የጥላቻ ንግግሮች ቸል የማይባሉ በመሆናቸው መንግሥት እያዘገጀ ያለው ሕግ የሚደገፍ ነው ይላሉ። ነገር ግን አዋጁ የመናገር ነጻነት፣ መረጃ የማግኘትና በሕገ-መንግስቱ የተደነገጉ መብቶችን የሚጋፋ እንዳይሆን ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። በተለይም በአዋጁ ውስጥ ለትርጉም የተጋለጡ ጉዳዮችን መልሶ ማየት እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም