አገራቱ የኢትዮጵያን የባሕር ኃይል የማቋቋምና የአየር ኃይሏን የማዘመን ትብብራቸውን ለማጠናከር ተስማሙ

52
ጥር 23/2012 (ኢዜአ) ኢትዮጵያና ፈረንሳይ የኢትዮጵያን የባሕር ኃይል ለማቋቋምና የአየር ኃይሏንም ለማዘመን ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር ተስማሙ። በመከላከያ ሚኒስትር ለማ መገርሳ የተመራና ከፍተኛ መኮንኖችን የያዘ የልዑካን ቡድን ከጥር 20 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በፈረንሳይ ጉብኝት እያደረገ ይገኛል። የመከላከያ ሚኒስትር ለማ መገርሳ ዛሬ ከፈረንሳዩ አቻቸው ፍሎረንስ ፓርሊ ጋር ተወያይተዋል። ከውይይቱ አስቀድሞም ለመከላከያ ሚኒስትሩ የክብር ዘብ አቀባበል ተደርጎላቸዋል። ሁለቱ አገራት የኢትዮጵያን የባህር ኃይል ለማቋቋምና የአየር ኃይሏን ለማዘመን ያላቸውን ትብብር ለማሳደግ መስማማታቸውን በፈረንሳይ ካለው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ሚኒስትሩ ከፕሬዚዳንት ፅህፈት ቤት የስራ ኃላፊዎችና ከፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ኤታ-ማዦር ሹም ከአዲሚራል በርናርድ ሮዤል ጋርም ተወያይተዋል። አቶ ለማ ከፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ጂን-ፓብቲስት ሌሞይኔ ጋርም ፓሪስ ላይ በሁለትዮሽ ግንኙነታቸው ዙሪያ መምከራቸው ይታወሳል። ኢትዮጵያና ፈረንሳይ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እ.አ.አ 1897 ነው። አገራቱ በቅርብ ዓመታት ውስጥ ያላቸውን ግንኙነት ማጠናከር የሚያስችሉ ጉብኝቶችን በመሪዎች መካከል እያካሄዱ ይገኛሉ። የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን መጋቢት 2011 ዓ.ም ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት ሁለቱ አገራት ወታደራዊ ትብብራቸውን ማጠናከር የሚያስችል ስምምነት መፈራረማቸውም ይታወሳል። በስምምነቱ መሰረት ፈረንሳይ ኢትዮጵያ ለምታቋቁመው የባሕር ኃይል ድጋፍ የምታደርግ ይሆናል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም