ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ የሥራ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁትን የቤልጂየም አምባሳደር አሰናበቱ

64
አዲስ አበባ ሰኔ19/2010 የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ የስራ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁትን የቤልጂየም አምባሳደር ጆሴፍ ኑድትሰንን አሰናብተዋል። ፕሬዝዳንቱ በጽህፈት ቤታቸው ከአምባሳደሩ ጋር በነበራቸው ቆይታ የሁለቱን አገራት ጠንካራ ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ መክረዋል። ተሰናባቹ አምባሳደር ባለፉት ሶስት ዓመታት በኢትዮጵያ በነበሩበት ወቅት የሁለቱን አገራት ግንኙነት ለማጠናከር በሰሩባቸው ሁኔታዎች ላይ  ለፕሬዝዳንት ሙላቱ ገለፃ ማድረጋቸውን ውይይቱን የተከታተሉት የፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት የፕሮቶኮልና የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አሸበር ጌትነት ተናግረዋል። በቤልጂየምና በኢትዮጵያ ያሉ ዩኒቨርሲቲዎች ትስስር በመፍጠር ጠቃሚ የምርምር ስራዎች መሰራታቸውንና ከቤልጂየም ዩኒቨርሲቲዎች የልምድ መቀስም ተግባራት እንደተከናወኑም ጭምር ነው አቶ አሸብር ያብራሩት። ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱም ኢትዮጵያና ቤልጂየም ለረጅም ዘመናት የዘለቀ ታሪካዊ ግንኙነት እንዳላቸው ጠቅሰው፤ በኢኮኖሚ መስክ ሊኖራቸው የሚገባው ግንኙነት የሚጠበቀውን ያክል የዳበረ አለመሆኑን መግለፃቸውን አቶ አሸብር ተናግረዋል። ይሁን እንጂ በቅርቡ የቤልጂየም ኩባንያዎች በኢትዮጰያ በጨርቃ ጨርቅና በቢራ ጠመቃ ሥራ ላይ ተሰማርተው ያሉ ቢሆንም ቤልጂየም ካላት እምቅ አቅም አንፃር ይህ አነስተኛ በመሆኑ ይህ ጉዳይ ተቀይሮ የአገሪቷ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች ተሰማርተው ቢሰሩ ውጤታማ እንደሚሆኑ ፕሬዝዳንቱ መግለፃቸውን አቶ አሸብር አስረድተዋል። አምባሳደር ጆሴፍ ኑድትስ በነበራቸው ቆይታ የኢትዮጵያና የቤልጂየምን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ሲሰሩ መቆየታቸውን በመግለጽ ቀጣይ እሳቸውን ተክተው ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡት አምባሳደርም በኢኮኖሚክ ዲፕሎማሲ ዘርፍ እንዲሰሩ እንደሚደረግም ገልፀዋል። በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታም ድጋፍ ላደረጉላቸው ለኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ምስጋና አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም