የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔን ለመዘገብ 320 የውጭ መገናኛ ብዙሃን ተመዝግበዋል

89
አዲስ አበባ  ጥር 23/2012 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ የሚካሄደውን የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ለመዘገብ እስካሁን 320 የውጭ መገናኛ ብዙሃን መመዝገባቸውን የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ገለጸ። 33ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ የካቲት 1 እና 2 ቀን 2012 ዓ.ም ይካሄዳል። ጉባዔውን ለመዘገብ በተለያዩ ክፍለ ዓለማት የሚገኙ መገናኛ ብዙሃን በየዓመቱ ወደ ኢትዮጵያ ይመጣሉ። ኢዜአ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ለዚሁ ተግባር የሚመጡ የውጭ መገናኛ ብዙሃንን ለማስተናገድ ስለተደረገው ዝግጅት ጠይቋል። የባለስልጣኑ የውጭ ሚዲያ ዘርፍ ዳይሬክተር አቶ መሐመድ ሰኢድ ለዘገባ ለሚመጡ የውጭ መገናኛ ብዙሃንን ለማስተናገድ ከአንድ ወር በፊት ስራ መጀመሩን ይገልጻሉ። በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስተባባሪነት የሚመራ ብሔራዊ ኮሚቴ መቋቋሙንና ባለስልጣኑም የራሱን ዕቅድ በማዘጋጀት የመገናኛ ብዙሃንን ጉዳይ በማስተባበር እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል። እስከ ትናንትና ባለው መረጃም 320 ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን የመሪዎቹን ጉባዔ ለመዘገብ ተመዝግበዋል። መገናኛ ብዙሃኑ ከአፍሪካ፣ አውሮፓ፣ እስያ፣ ላቲን አሜሪካና ሰሜን አሜሪካ አህጉራት የተወጣጡ እንደሆኑም ጠቁመዋል። በአፍሪካ ኅብረት የኦንላይን ምዝገባ ያካሄዱ መገናኛ ብዙሃን ዝርዝር ለባለስልጣኑ መላኩንም አቶ መሐመድ አስረድተዋል። ባለስልጣኑ በበኩሉ የመገናኛ ብዙሃኑ ባለሙያዎች ቪዛ እንዲያገኙ ለኢሚግሬሽን ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ ስም ዝርዝራቸው መላኩን አውስተዋል። ይዘዋቸው የሚመጡ የሙያ መሳሪያዎች መግባት እንዲችሉ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ለሚገኘው የጉምሩክ ጽህፈት ቤት የትብብር ደብዳቤ እንዲጻፍላቸው እየተደረገም ነው። ወደ ኅብረቱ መሰብሰቢያ አዳራሽ ሲመጡ የዘገባ ፈቃድ እንዲያገኙ በኅብረቱ ቅጥር ግቢ ለተዘጋጀው የባጅ ማዕከል ስም ዝርዝራቸው ተልኳል። በአጠቃላይ ባለስልጣኑ መገናኛ ብዙሃኑ የዘገባ ፈቃድ አግኝተው ስራቸውን በጥሩ ሁኔታ እንዲከውኑ የማመቻቸት ስራ እየሰራ መሆኑን ነው አቶ መሐመድ የገለጹት። መገናኛ ብዙሃኑ በባለስልጣኑ አገልግሎት ለማግኘት የአፍሪካ ኅብረት ባዘጋጀው የኦንላይን ምዝገባ ስርዓት መመዝገባቸውን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ከፓስፖርት ጋር፣ የሙያ መሳሪያ ማመልከቻቸውንና የወከሉትን መገናኛ ብዙሃን በግልጽ የሚያሳይ መረጃ ማቅረብ አለባቸው ብለዋል። ባለስልጣኑም ይህን መሰረት አድርጎ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግላቸው አክለዋል። የመገናኛ ብዙሃኑ ባለሙያዎች ወደ አዲስ አበባ ከመጡ በኋላ ያለ ምንም ገደብና እክል ስራቸውን በነጻነት እንዲከውኑና ችግር ቢያጋጥማቸው ፈጥኖ እንዲፈታላቸው እንደሚያደርግ ነው አቶ መሐመድ ያስረዱት። ጉባዔው የሚካሄድበት ወቅት ሲቃረብ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ መገናኛ ብዙሃን ቁጥር የሚጨምር በመሆኑ አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል። ያለፈውን ዓመት የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ የዘገቡ መገናኛ ብዙሃን ቁጥር 480 ነበር። ዘንድሮ ይህ ቁጥር እንደሚጨምር ይጠበቃል ያሉት አቶ መሐመድ ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን የተውጣጡ ከ350 በላይ ባለሙያዎችም ጉባዔው እንደሚዘግቡ ይጠበቃል ብለዋል። 33ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ "የጥይት ድምጽ የማይሰማባትን አህጉር እውን በማድረግ ለአፍሪካ ልማት ምቹ ሁኔታ እንፍጠር" በሚል መሪ ሃሳብ ነው የሚካሄደው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም