254 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያለው የገናሌ ዳዋ 3 የሃይል ማመንጫ በሚቀጥለው ሳምንት ይመረቃል

79
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 22/2012 254 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያለው የገናሌ ዳዋ ሶስት የውሃ ሀይል ማመንጫ በሚቀጥለው ማክሰኞ እንደሚመረቅ ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል አስታወቀ። ለግድቡ ግንባታ 451 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ተደርጓል። የኢትዮጵያ  ኤሌክትሪክ ሃይል ኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ''የሃይል ማመንጫው 254 ሜጋ ዋት በዓመት እንደሚያመርትና ይህም በገንዘብ ሲሰላ በቀን እስከ 4 ሚሊዮን ብር ማግኘት የሚያስችል ነው'' ብለዋል። ''ሙሉ ለሙሉ ወደስራ ሲገባ 254 ሜጋዋት ያመነጫል ተብሎ የሚጠበቀው ግድቡ፤ እያንዳንዳቸው 84 ነጥብ 7 ሜጋዋት ማመንጨት የሚችሉ ሶስት ተርባይኖች አላቸው'' ብለዋል የሃይል ማመንጫው የተገነባው ዝናባማ በሆነው በኦሮሚያ ክልል በጉጂና ባሌ ዞንኖች መካከል መሆኑ የማመንጨት አቅሙን ቋሚና የተሻለ እንደሚያደርገው ተናግረዋል። የፕሮጀክቱ ተመርቆ ወደስራ መግባት እያደገ የመጣውን የሃይል ፍላጎት ከአቅርቦቱ ጋር ለማጣጣም የሚያግዝ እንደሚሆን ገልጸዋል። የፕሮጀክቱ ግንባታ በአጠቃላይ 451 የአሜሪካ ዶላር የፈጀ ሲሆን 40 በመቶ በመንግስት ቀሪው 60 በመቶ ከቻይና ኤግዚም ባንክ በተገኘ ብድር የተገኘ ነው። ''የፕሮጀክቱ በአራት አመት እንዲጠናቀቅ ውል ታስሮ በ2003 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን የግንባታው አካል የሆነ 2 ኪሎሜትር ዋሻ መቆፈር ስለነበረበትና በቁፋሮው ወቅት ከመሬቱ ተፈጥሮ ጋርና ከሚያጋጥሙ አለቶች እንዲጓተት አንድ ምክንያት ሆኗል'' ብለዋል። ከዚህ በተጨማሪ ከካሳ አከፋፈል ጋር በተያያዘ በግንባታው ምክንያት ካሳ የሚያስፈልጋቸውን ከማያስፈልጋቸው ጋር የመቀላቀል ሁኔታ በማጋጠሙ አጣርቶ ችግሩን ለመፍታት ጊዜ መውሰዱንም ተናግረዋል። የኢትዮጵያ የውሃ ተፋሰስ እስከ 45 ሽህ ሜጋ ዋት ሃይል ለማመንጨት አቅም እንዳለው የሚተገመት ሲሆን በአሁኑ ወቅት እየተመረተ ያለው ሃይል 4 ሺህ 400 ሜጋ ዋት ነው። ይህም ከ15 የውሃ፣3 የንፋስ፣ አንድ የደረቅ ቆሻሻና አንድ የእንፋሎት በድምሩ ከ20 የሃይል ማመንጫዎች ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም