የአፍሪካ ግብርና ትራንስፎርሜሽን  መርሐግብር  አፈጻጸም  በመጪው የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ይገመገማል

74

ጥር 22/2012 (ኢዜአ) እ.ኤ.አ በ2014 ይፋ የተደረገው የአፍሪካ ግብርና ትራንስፎርሜሽን  መርሐግብር  አፈጻጸም  በመጪው የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ላይ እንደሚገመገም  ተገለጸ፡፡

የግብርና ትራንስፎርሜሽን መርሐግበሩ በአፍሪካ ውስጥ ለሚካሄደው የግብርና ምርታማነትና ምጣኔ ሃብታዊ እድገት አብዮታዊ መሳርያ እንደሚሆንም ታምኖበታል፡፡

በቅረቡ በአዲስ አበባ በሚካሄደው የአፍሪካ ህብረት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ከአምስ አመት በፊት በ2014 በኢኳቶሪያል ጊኒ ማላቦ ይፋ በተደረገው የግብርና ትራንስፎርሜሽን መርሐግበር ላይ የውጤት ግምገማ የሚደረግ ሲሆን ሁለተኛው ዙር የግብርና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ቀርቦ ይፋ ይሆናል ተብሏል፡፡

የግብርና ትራንስፎርሜሽን መርሐግብሩ  የህብረቱ አባል አገራት በግብርናው ዘርፍ ያላቸውን ምርታማነት  የሚያስተሳስሩበትና ወደ ብልጽግና የሚያመሩበት የጋራ ዕቅድ መሆኑም ተመልክቷል፡፡

የወቅቱ  የአፍሪካ ግብርና ልማት አጠቃላይ ፕሮግራም መሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አጠቃለይ የአምስት አመቱን የግብርና ትራንስፎርሜሽን አፈጻጸም በተመለከተ በህብረቱ ስብሰባ ላይ ሪፖርት እንደሚያቀርቡም ተገልጿል፡፡

መርሐግበሩ በአፈሪካ አባል አገራት መሪዎች አስፈጻሚነት የሚተገበር ሲሆን ከዚህ በፊት እ.ኤ.አ በ2017 የአፈጻጸም ግምገማ በተደረገበት ወቅት ከ47 የአፍሪካ አገራት ሃያ ሀገራት ብቻ ዕቅዱን በተፈለገው ልክ ማሳካት መቻላቸውን ከአፍሪካ ህብረት ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም