የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን እሑድ የመልስ ጨዋታውን ከቡሩንዲ አቻው ጋር ያደርጋል

75

አዲስ አበባ፤ ጥር 22/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከነገ በስቲያ የፊፋ የዓለም ዋንጫ የቅድመ ማጣሪያ የመልስ ጨዋታውን ከቡሩንዲ አቻው ጋር በባህርዳር ስታዲየም ያደርጋል። በነሐሴ 2012 ዓ.ም ፓናማ እና ኮስታሪካ በጋራ የሚያዘጋጁት 10ኛው የፊፋ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ዓለም ዋንጫ ይካሄዳል።

በውድድሩ ለመሳተፍ የአፍሪካ ዞን የማጣሪያ ጨዋታ ከሁለት ሳምንት በፊት የተጀመረ ሲሆን የመልስ ጨዋታዎች በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ይካሄዳሉ።

በዚሁ መሰረት የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ጥር 24/2012 ዓ.ም በባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ከብሩንዲ አቻው ጋር ከቀኑ 10 ሠዓት የመልስ ጨዋታቸውን ያደርጋል።

ጥር 9 ቀን 2012 ዓ.ም በኢንትዋሪ ስታዲየም በተደረገ ጨዋታ በአሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል የሚሰለጥነው ብሔራዊ ቡድን ተጋጣሚውን 5 ለ 0 በሆነ ሰፊ ውጤት ማሸነፉ ይታወሳል።

ምርቃት ፈለቀ፣ ታሪኳ ዴቢሶ፣ አረጋሽ ካልሳ፣ ረድኤት አስረሳኸኝ እና የቡሩንዲዋ የተከላካይ መስመር ተጫዋች ኬዛ አንጄሊክ በራሷ ግብ ላይ ባስቆጠሯቸው ግቦች ነው ብሔራዊ ቡድኑ ማሸነፍ የቻለው።

በአሰልጣኝ ፍሬው የሚሰለጥነው ብሔራዊ ቡድን በመጀመሪያ ዙር ያስመዘገበው ውጤት እግሩን ወደ ቀጣዩ ዙር ያስገባበት እንደሆነ ያመለክታል።

በአንጻሩ በ36 ዓመቱ ቡሩንዳዊ አሰልጣኝ ጆስሊን ቢፕፉቡሳ የሚሰለጥነው የብሩንዲ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ወደ ቀጣዩ ዙር የማለፍ ዕድሉን በሜዳው አሳልፎ ሰጥቷል።

25 የልዑካን ቡድን የያዘው የቡሩንዲ ብሔራዊ ቡድን ዛሬ አዲስ አበባ እንደሚገባ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ባህሩ ጥላሁን ለኢዜአ ገልጸዋል።

ቡድኑ ዛሬውኑ ጨዋታው ወደሚካሄድበት ባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም እንደሚያመራም ተናግረዋል።

የሁለቱን ብሔራዊ ቡድኖች ጨዋታ ታንዛኒያዊያን ዳኞች እንደሚመሩትም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን በደርሶ መልስ ውጤት ካሸነፈ በቀጣዩ ዙር ከሁለት ወር በኋላ ከዚምባቡዌና ማላዊ አሸናፊ ጋር የሚጫወት ይሆናል።

ዚምባቡዌና ማላዊ በማላዊ ካሙዙ ስታዲየም ያደረጉት የመጀመሪያ ጨዋታ 1 ለ 1 በሆነ የአቻ ውጤት የተጠናቀቀ ሲሆን የመልሱ ጨዋታ ነገ በባርቡርፊልድስ ስታዲየም ከቀኑ 10 ሠዓት ላይ ይካሄዳል።

በመጪው ነሐሴ ፓናማ እና ኮስታሪካ በጋራ በሚያዘጋጁት 10ኛው የፊፋ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ዓለም ዋንጫ 16 ብሔራዊ ቡድኖች ይሳተፋሉ።

በሌላ የእግር ኳስ ዜና የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 12ኛ ሳምንት ጨዋታዎች የፊታችን እሁድና ሰኞ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ይካሄዳሉ።

ቅዱስ ጊዮርጊስ  ከነገ በስቲያ በአዲስ አበባ ስታዲየም ከቀኑ በ9 ሠዓት ሲዳማ ቡናን ያስተናግዳል።

እሁድ ጥር 24 ቀን 2012 ዓ.ም ደግሞ በክልል ከተሞች አምስት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ።

በጅማ ስታዲየም ጅማ አባ ጅፋር ከመቐለ ሰብዓ እንደርታ፣ በትግራይ ስታዲየም ስሑል ሽረ ከሐዋሳ ከተማ፣ በሶዶ ስታዲየም ወላይታ ድቻ ከድሬዳዋ ከተማ፣ በዝዋይ ሼር ሜዳ ወልቂጤ ከተማ ከባህርዳር ከተማ እና በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም አዳማ ከተማ ከኢትዮጵያ ቡና በተመሳሳይ ከቀኑ በ9 ሠዓት ይጫወታሉ።

ሰኞ ጥር 25 ቀን 2012 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስታዲየም ከቀኑ 10 ሠዓት ሰበታ ከሀዲያ ሆሳዕና፣ በአፄ ፋሲለደስ ስታዲየም ፋሲል ከነማ ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከቀኑ በ9 ሠዓት ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ፣ ስሑል ሽረ፣ ሰበታ ከተማና ወልቂጤ ከተማ በስታዲየም እድሳት ምክንያት ጨዋታቸውን በሌላ ሜዳ እያደረጉ ይገኛሉ።

የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ መቐለ ሰብዓ እንደርታ በ22 ነጥብ ሲመራ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ20 ፋሲል ከነማ በ19 ነጥብ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል።

ወላይታ ድቻ፣ ጅማ አባ ጅፋርና ሀዲያ ሆሳዕና ከ14ኛ እስከ 16ኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ።

የፕሪሚየር ሊጉን ኮከብ ግብ አግቢነት የፋሲል ከነማው ሙጂብ ቃሲም በ10 ግቦች ሲመራ፣ የሲዳማ ቡናው አዲስ ግደይ በ7 ግቦች እንዲሁም የባህርዳር ከተማው ፍጹም አለሙ፣ የመቐለ ሰብዓ እንደርታው አማኑኤል ገብረሚካኤልና የሀዋሳ ከተማው ብሩክ በየነ በተመሳሳይ 6 ግቦች ይከተላሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም