የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ኦዲት ሪፖርት ከአፍሪካ አገሮች የተሻለ ነው

93

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 22/2012 የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን በኦዲት ሪፖርት ከአፍሪካ አገሮች  የተሻለ አፈጻጸም እንዳስመዘገበ ተገለጸ።

የኦዲት ሪፖርት አፈጻጸም ምዘናው የተካሄደው በመላው አለም አገሮች ላይ ነው።

ባለስልጣኑ ከአፍሪካ አገሮች መካከል ቀዳሚ ሆኖ ሲገኝ የአሁኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

የዓለም አቀፉ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ለአንድ ሳምንት በኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ውስጥ ባሉ የተለያዩ ክፍሎች ኦዲት አድርጎ ባቀረበው ሪፖርት ባለስልጣኑ 91 ነጥብ 78 ከመቶ ውጤት ማምጣቱን አስታውቋል።

ባለስልጣኑ የተገኘውን ውጤት አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ፤ ኦዲተሮቹ በዋናነት የባለስልጣኑን የአሮፕላን ምዘናና አግባብነት የሰርተፊኬት አሰጣጥ፣ የኤርናቪጌሽን ቁጥጥር፣ የኤሮድሮም ሴፍቲ እና ስታንዳርድ፣ የሰው ሀይል ስልጠናና ሌሎች መሥፈርቶች መዝነው ነጥብ ሰጥተዋል።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ተወካይ አቶ ሽመልስ ገብረዓብ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ባለስልጣኑ የዓለም አቀፉን የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት መስፈርቶችን በማሟላቱ ከፍተኛ ውጤት አስመዝግቧል።

አቪዬሽኑ በኦዲት ሪፖርት አፈጻጸም ከአፍሪካ አገሮች የቀዳሚነት ስፍራ ለመያዝ መብቃቱንም ገልጸዋል።

ውጤቱን በማስቀጠልና የተሻለ የኦዲት ሪፖርት አፈጻጸም ላይ በመድረስ በየጊዜው አያደገ የመጣውን የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ጋር ተወዳዳሪ ሆኖ መቀጠል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ከ75 ዓመት በፊት በ1937 ዓ.ም የተቋቋመ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም