ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኤርትራን ልዑካን ተቀበሉ

106
አዲስ አበባ ሰቤ 19/2010 የኤርትራ መንግሥት የልዑካን ቡድን በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ አቀባበል ተደረገለት። የልዑካን ቡድኑ አባላት በአዲስ አበባ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ ምሁራን፣ የኃይማኖት አባቶች፣ አትሌቶችና አርቲስቶች የተሳተፉበት ቡድን ወንድማዊ አቀባበል አድርጎላቸዋል። የኢህአዴግ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ግንቦት 2010 ዓ.ም በሁለቱ ወንድማማች ሕዝቦች መካከል ለዓመታት የዘለቀው አለመግባባት እልባት አግኝቶ ዘላቂ ሰላም ለመፍጠር ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል። የኢትዮ-ኤርትራ መልካም ግንኙነት ለቀጠናው ሰላም የጎላ ሚና እንዳለው በመገምገም ኢትዮጵያ የአልጀርሱን ስምምነት ለመተግበር ተስማምታለች። የኤርትራ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂም ከቀናት በፊት የሰላም ጥሪውን ተቀብለው በዛሬው ዕለት የአገሪቱን ልዑካን ወደ ኢትዮጵያ ልከዋል። ይህም ለበርካታ ዓመታት ተቋርጦ ለቆየው የሁለቱ አገራት ግንኙነት አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ መለስ ዓለም እንዳሉት የሁለቱ አገራት ግንኙነት መሻሻል ለቀጠናውና መላው አፍሪካ ጭምር የሰላም አስተዋፅኦ ይኖረዋል። በሁለቱ አገራት መካከል የተደረገው ውይይት በሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች መካከል ዳግም የሰላም አየር እንዲነፍስ በማድረግ አዲስ የግንኙነት ምዕራፍ እንደሚከፍት ይጠበቃል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም