የመከላከያ ሚኒስትር ለማ መገርሳ እና የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ጂን-ፓብቲስት በፓሪስ መከሩ

135
አዲስ አበባ ጥር 21/2012  (ኢዜአ) የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስትር ለማ መገርሳ ከፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ጂን-ፓብቲስት ሌሞይኔ በሁለትዮሽ አገራዊ ጉዳዮች ላይ በፓሪስ መከሩ። ከፍተኛ የአገር መከላከያ ሰራዊት አመራሮችን በማካተት በመከላከያ ሚኒስትር ለማ መገርሳ የሚመራ የልዑካን ቡድን ከትናንት ጀምሮ በፈረንሳይ ጉብኝት በማድረግ ላይ ይገኛል። የመከላከያ ሚኒስትሩ ለማ መገርሳ ከፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ጂን-ፓብቲስት ሌሞይኔ በፓሪስ በሁለትዮሽ ግንኙነታቸው ዙሪያ መክረዋል። የሁለቱ አገራት ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ባደረጉት ውይይት አገራቱ ያላቸውን ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር የሚያሰችሉ ስራዎችን ለማከናወን ስምምነት ላይ መድረሳቸውን በፈረንሳይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስታውቋል። የጉብኝቱ አላማ ኢትዮጵያና ፈረንሳይ በአየርና ባህር ሃይል ስልጠና እና ወታደራዊ የቁሳቁስ አቅርቦትን በተመለከተ ትብብራቸውን ማጠናከር አላማ ያደረገ መሆኑ ታውቋል። የመከላከያ ሚኒስትሩ በፈረንሳይ ቆይታቸው ከፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት ሃላፊዎች እና ከፈረንሳይ የጦር ሃይል ዋና አዛዥ ፍራንስዋ ሌኮይንትሬ ጋር ይወያየሉ ተብሎ ይጠበቃል። ኢትዮጵያና ፈረንሳይ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እ.አ.አ 1897 ነው። ሁለቱ አገራት በቅርብ ዓመታት ውስጥ ያላቸውን ግንኙነት ማጠናከር የሚያስችሉ ጉብኝቶችን በአገራቱ መሪዎች መካከል እያካሄዱ ይገኛሉ። የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በመጋቢት 2011 ዓ.ም ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት ሁለቱ አገራት በወታደራዊ መስክ ያላቸውን ትብብር ማጠናከር የሚያስችል ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል። በስምምነቱ መሰረት ፈረንሳይ ኢትዮጵያ ለምታቋቁመው የባህር ሃይል ድጋፍ የምታደረግ ይሆናል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም