በቻይና ናጂንግ ሊካሄድ የነበረው የዓለም የቤት ውስጥ ውድድር በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ተራዘመ

128
ጥር 21/2012 (ኢዜአ) የዓለም አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በኮሮና ቫይረስ ምክንያት በቻይና የሚካሄደውን የዓለም የቤት ውስጥ ውድድር ማራዘሙን አስታወቀ። 18ኛው የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ውድድር በመጋቢት ወር 2012 ዓ.ም በቻይና ናጂንግ ከተማ እንዲካሄድ ቀጠሮ ተይዞ ነበር። በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ በተስፋፋው የኮሮና ቫይረስ ምክንያት ውድድሩን በተባለለት ጊዜ ማካሄድ አስቸጋሪ ሆኗል። በመሆኑም ውድድሩ በሚቀጥለው ዓመት ማለትም እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2021 ለማካሄድ ታስቧል። የዓለም አትሌቲክስ ቻይና የኮሮኖ ቫይረስን ለመከላከል እያደረገች ያለችውን ጥረት እየተከታተለ እንደሆነና ተቋሙ አገሪቷ እያከናወነች ላለው ስራ ድጋፍ እንደሚያደርግም ጠቅሷልል። ቫይረሱን አስመልክቶ ለአትሌቶች፣ ለብሔራዊ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖችና አጋሮች በፍጥነት እየተለዋወጡ ያሉ ጉዳዮችን ማሳወቅ ተገቢ እንደሆነም አመልክቷል። የዓለም አትሌቲክስ የጤና ቡድን ከዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት ጋር በቻይናና ከቻይና ውጪ በሌሎች አገራት የኮሮኖ ቫይረስን አስመልክቶ በቅርበት መረጃዎችን በመለዋወጥ ባገኘው መረጃ ኮሮና ቫይረስ አሳሳቢ ደረጃ ላይ የሚገኝ እንደሆነ ለመረዳት መቻሉን ነው የገለጸው። የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ውድድሩን በሌሎች አገራት ለማድረግ አስቦ እንደነበር ያስታወቀው ፌዴሬሽኑ ቫይረሱ ከቻይና ውጪ ወደ ሌሎች አገራት የመሰራጨቱ ጉዳይ አሳሳቢ ስለሚሆን አገር የመቀየር ምርጫውን መሰረዙን አመልክቷል። ብዙ አትሌቶች ውድድሩ እንዲካሄድ ካላቸው ፍላጎት አንጻርም የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ውድድሩን ሙሉ ለመሉ የመሰረዝ ምርጫውንም እንደተወውም ነው ተጠቀሰው። ይህ በመሆኑ ምክንያት ናንጂንግ እ.አ.አ በ2021 ውድድሩን የሚካሄድበት ምቹ ጊዜ ማግኘት እንደምትችል ነው የዓለም አትሌቲክስ ያስታወቀው። ናንጂንግ እ.አ.አ በ2017 በዓለም አትሌቲክስ ውድድሩን እንድታዘጋጅ መመረጧ ይታወሳል። የዓለም አትሌቲክስ ከአትሌቶች፣ ከናንጂንግ የውድድር አዘጋጅ ኮሚቴና ከአጋሮች ጋር የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ውድድር እ.አ.አ 2021 የሚካሄድበት ቀን ለመወሰን በቅርበት እንደሚሰራም አስታውቋል። የእስያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በኮሮና ቫይረስ ምክንያት በየካቲት ወር 2012 ዓ.ም በቻይና ሀንግዙ ግዛት ሊካሄድ የነበረውን ዘጠነኛው የእስያ የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ውድድር መሰረዙን ከሶስት ቀናት በፊት ማስታወቁ ይታወሳል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም