ሜክሲኮ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የንግድ፣ ቱሪዝምና አቪየሽን ግንኙነት ማጠናከር ትፈልጋለች

69
ጥር፣ 21/2012 (ኢዜአ) ሜክሲኮ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የንግድ፣ ቱሪዝምና አቪየሽን እንደሁም የሁለትዮሸ ግንኙነቱን ማጠናከር እንደምትፈልግ የአገሪቱ አምባሳደር ገለጹ። በኢትዮጵያ የሜክሲኮ አምባሳደር ቪክቶር ትሪቪኖ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ሁለቱ አገሮች በተለያዩ ዘርፎች የቆየና ጠንካራ ግንኙነት እንዳላቸው አውስተዋል። ኢትዮጵያና ሜክሲኮ ዲፕሎማሲያ ግንኙነት ከጀመሩ 70 አመታትን ማስቆጠራቸውን ገልጸው "ኢትዮጵያ ለኛ በጣም አስፈላጊ አገር ናት" ብለዋል። በቀጣይ የሁለቱን አገሮችን ጠንካራ ግንኙነት በመጠቀም በንግድና ቱሪዝም ዘርፍ ትብብራቸውን ለማጠናከር እንደሚሰሩም ገልጸዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሜክሲኮ የጀመረውን የጭነት በረራ አገልግሎት እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የንግድ ግንኙነትን ለማሳደግ እንደሚሰሩም አምባሳደሩ ተናግረዋል። እንደ አምባሳደሩ ገለጻ የአቪየሽን ዘርፍ ሜክሲኮ ከኢትዮጵያ ጋር መስራት ከምትፈልግባቸው ዘርፎች መካከል አንዱ ነው። ሜክሲኮ ከዓለም ቀዳሚ የቱሪዝም መዳረሻ ከሆኑ አስር አገሮች መካከል መሆኗን ጠቅሰው ኢትዮጵያም ይህንን ማሳካት የሚያስችሉ በርካታ የቱሪስት መዳረሻዎች አሏት ብለዋል። ለዚህም ሜክሲኮ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን አረጋግጠዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቀጣይ ወደ ሜክሲኮ የመንገደኞች የበረራ አገልግሎት ሲጀምር ኢትዮጵያና ሜክሲኮን ለሚጎበኙ ቱሪስቶች መልካም አጋጣሚ ይሆናልም ነው ያሉት። በሌላ በኩል ሁለቱ አገሮች በቀጠናዊና አለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር እየሰሩ መሆኑን ጨምረዋል። ኢትዮጵያ በጎረቤት አገሮች ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን እያደረገች ያለውን ጥረት ያደነቁት አምባሳደር ትሪቪኖ ሜክሲኮም ተመሳሳይ ተግባር እያከናወነች መሆኑን ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገሮች ጋር በልማትና ሰላም መፍጠር ጉዳዮች በትብብር መስራቷ ለአካባቢው አገሮች ጉልህ አስተዋጽኦ አለው ነው ያሉት። ኢትዮጵያ ከሜክሲኮ ጋር እንደ ጎርጎሮሳውያን አቆጣጠር በ1949 ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በመጀመር ከአፍሪካ አገራት ቀዳሚዋ መሆኗን መረጃዎች ያሳያሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም