የወጪና ገቢ ንግድ ሚዛንን ለማስጠበቅ እየሰራ መሆኑን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አመለከተ

101
አዲስ አበባ  ኢዜአ ጥር20/2012 በወጪና በገቢ ንግድ መካከል ያለውን ሰፊ የንግድ ሚዛን ልዩነት ለማጥበብ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገለጸ። ሚኒስቴሩ የግማሽ አመት የወጭ ንግድ አፈጻፀሙን በተመለከተ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል። ሚኒስቴሩ በመግለጫው እንዳመለከተው፤ በወጪ  ንግድና በገቢ ንግድ መካከል ያለው ልዩነት እጅግ ሰፊ ነው። የሚኒስቴሩ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተሩ አቶ ወንድሙ ፍላቴ '' በወጪና በገቢ ንግድ መካከል ያለውን ልዩነት ለማጥበብና የገቢ ሸቀጦችን በአገር ውስጥ ምርት ለመተካት የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ ነው'' ብለዋል። የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ግንባታ፣ የአገር ውስጥ ባለሃብቶችን የፋናንስ ችግር መፍታትና የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰትን ማሳደግ ላይ ትኩረት በመስጠት እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል። ሚኒስቴሩም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር የዘርፉን ችግር ለመፍታት አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ አቶ ወንድሙ ገልጸዋል። በተለይም ላኪዎች የሚያጋጥማቸውን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለመፍታት የህግ ማሻሻያ ማድረግን ጨምሮ በመንግስት በኩል የተለያዩ ርምጃዎች እየተወሰዱ እንደሆነ ተናግረዋል። በዚህም ላኪዎች እንደየደረጃቸው የውጭ ምንዛሬ ፍላጎታቸው እንዲሟላ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አመልክተው፤ የቀረጥ ማሻሻያ እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል። ለአብነትም በቆዳና ቆዳ ውጤቶች ወጪ ንግድ ላይ ተጥሎ የነበረ ቀረጥ ላይ ማሻሻያ መደረጉ ውጤት ማምጣቱን ገልጸዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም