የደም ዋጋ የተከፈለበትን የካቲት 11 ደም በመለገስ እንዲከበር ትዴፓ ጥሪ አቀረበ

82

አዲስ አበባ ኢዜአ፤ጥር 20/2012 የደም ዋጋ የተከፈለበትን የካቲት 11 በጭፈራና ድግስ ሳይሆን ደም በመለገስ እናክብረው ሲል የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) ጥሪ አቀረበ።

በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የካቲት 11 የህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ (ህወሃት)  መስረታ የሚታወስባት እለት ናት።

ፓርቲው በዚሁ እለት ከ45 ዓመት በፊት የትጥቅ ትግሉን አሃዱ ብሎ የጀመረ ሲሆን፤ ቀኑም በፓርቲው አባላትና ሌሎች ደጋፊዎች በየዓመቱ በተለያዩ ሁነቶች ይከበራል።

ዘንድሮም የፓርቲውን 45ኛ ዓመት ምስረታ በዓል በልዩ ሁኔታ ለማክበር ከወዲሁ ዝግጅት መጀመሩ እየተገለጸ ነው።

የትዴፓ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሙሉብርሃን ሃይሌ እለቱን አስመልክቶ በተለይ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በ17 ዓመቱ የትጥቅ ትግል በርካቶች ለሰላም፣ ዴሞክራሲና ልማት ውድ ህይወታቸውን ሰጥተዋል።

ነገር ግን  በተከፈለው መስዋትነት ልክ ውጤት ማስመዝገብ አለመቻሉን ነው የገለጹት።

ልማትና ዴሞክራሲን በማስፈን መተኪያ የሌለው ህይወታቸውን የገበሩ ሰማዕታትን መካስ እንደሚገባ በመጠቆም።

ለክልሉ ህዝብ ፍትህና ዴሞክራሲ  የሚታገለው የትዴፓ ለእለቱ ልዩ ክብር እንዳለውም ኃላፊው ተናግረዋል።

ፓርቲያቸው በእለቱ  ደም በመለገስ የተከፈለውን የደም ዋጋ እንደሚያስብ ገልጸው፤ በመሆኑም ኢትዮጵያዊያን በዕለቱ የደም ልገሳ በማድረግ ቀኑን እንዲያስቡት ጥሪ አቅርበዋል።

"ደማችን ብሔር፣ ኃይማኖትና ዘር ሳይለይ ለተጎዱ ሁሉም ወገኖቻችን ይሆናል" ሲሉ በመግለጽ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም