በሶኮሩ በሚገኝ የሀይል ማስተላለፊያ ላይ የእሳት አደጋ ደርሷል

83
አዲስ አበባ ሰኔ 19/2010 በኦሮሚያ ክልል ጅማ ዞን ሶኮሩ ወረዳ በሚገኝ የሀይል ማስተላለፊያ (ትራንስፎርመር) ላይ የእሳት አደጋ ደርሷል። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የውጭ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ምስክር ነጋሽ በግልገል ጊቤ አንድና ሁለት መካከል በጅማ ዞን ሶኮሩ በሚገኝ ባለ 400 እና 230 ኪሎ ቮልት ከፍተኛ የኤሌትሪክ ማከፋፈያ ጣቢያ ውስጥ በሚገኝ ባለ 250 ሜጋ ዋት ትራንስፎርመር ላይ የእሳት አደጋ መድረሱን ለኢዜአ ገልጸዋል። በአሁኑ ሰአት በትራንስፎመሩ ላይ የተከሰተውን የእሳት ቃጠሎ ለማጥፋት የኢትዮጵያ ኤሌትሪክ ሃይል ባለሙያዎች ከጅማ የእሳት አደጋና መቆጣጠሪያ ማዕከል ባለሙያዎች ጋር በመሆን ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ነው ብለዋል። የትራንስፎርመሩን መቃጠል በሆሳዕና፣ በጅማ፣ አጋሮ፣ ቦንጋና ሚዛን ቴፒ የኤሌትሪክ መቋረጥ ማስከተሉን ገልጸዋል። የእሳት አደጋው መንስኤ የቴክኒክ ችግር እንደሆነ አቶ ምስክር ጠቁመዋል። እስካሁን ባለው መረጃ በእሳት አደጋው በሰው ላይ ምንም አይነት ጉዳት እንዳልደረሰ አመልክተዋል። በሶኮሩ የሃይል ማስተላለፊያ በተቃጠለው ትራንስፎርመር ምትክ ሌላ ትራንስፎርመር እንደሚገኝና ትራንስፎርመሩ እስኪተከል ጥቂት ቀናት እንደሚፈጅና ህብረተሰቡ ይህን ተገንዝቦ በትዕግስት እንዲጠባበቅ አስገንዝበዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም