በፍትህ እጦት ለዓመታት ያጣነውን የእርሻ መሬት በማግኘታችን ተደስተናል.....በጎንደር ዙሪያ ወረዳ አርሶ አደሮች

83
ጎንደር ሰኔ19/2010 የእርሻ መሬት ተወስዶባቸው ለበርካታ ዓመታት ያጡትን ፍትህ በአሁኑ ወቅት በማግኘታቸው መደሰታቸውን በጎንደር ዙሪያ ወረዳ የሚኖሩ ሴት አርሶአደሮች ገለጹ። በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ከህግ አግባብ ውጪ በህገ-ወጥ ግለሰቦች የመሬት ወረራ የእርሻ መሬታቸው ተወስዶባቸው ለነበሩ 242 አቅመ ደካሞች፣ ሴቶች፣ ህጻናትና አረጋዊያን የማስመለስ ሥራ ማከናወኑን የዞኑ የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም መምሪያ አስታውቋል፡፡ አርሶአደር ሻሼ አሰፋ በወረዳው የገብርኤል ገጠር ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ ከ24 ዓመት በፊት ባለቤታቸው ያወረሷቸውን ግማሽ ሄክታር የእርሻ መሬት በጉልበተኛ ግለሰብ ተቀምተው ፍትህ አጥተው መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡ "የልጆቼ ማሳደጊያ የነበረው የእርሻ መሬት በአንድ ህገ-ወጥ ግለሰብ አላግባብ በመወሰዱ ላላፉት ዓመታት ልጆቼን በችግር ውስጥ ሆኜ ለማሳደግ ተገድጄ ቆይቻለሁ" ብለዋል፡፡ "ፍትህ ለማግኘት ያልደረስኩበት ተቋም አልነበረም ያሉት" አርሶ አደር ሻሼ ዘንድሮ ፍትህ በማግኘት የተነጠቁትን የእርሻ መሬት ስለተመለሰላቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል ፡፡ "የሕዝቡን የመልካም አስተዳደር እጦት ችግር ለመፍታት የምኖርበት የገጠር ቀበሌ አስተዳደር እኔን መሰል ድሆች ፍትህ እንድናገኝ በማድረጉ ደስታዬ ወደር የለውም ሲሉ" ተናግረዋል፡፡ "ከባለቤቴ ጋር ፍቺ ስፈጽም በተካፈልኩት የእርሻ መሬት ላይ ለአራት ዓመታት በፍትህ እጦት ውሳኔ አልባ በደል ደርሶብኝ ቆይቷል" ያሉት ደግሞ የእዚሁ ወረዳ ነዋሪ ሴት አርሶ አደር ታድፋለች ዘውዱ ናቸው፡፡ በዚህ ዓመት ወረዳው ባደረገው ዳግም የማጣራት ሥራ ከባለቤታቸው ጋር የተካፈሉት ሩብ ሄክታር መሬት ተመልሶላቸው ህጋዊ የመሬት ባለቤትነት የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር ማግኘታቸውንና ይህም እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል፡፡ በጎንደር ዙሪያ ወረዳ የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ጽህፈት ቤት የገጠር መሬት አስተዳደር ቡድን መሪ አቶ አደራጀው ጎንፋ በበኩላቸው በገጠሩ ክፍል በመሬት ጉዳይ የሚታየውን የመልካም አስተዳደር ችግር ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። በተያዘው ዓመት መሬታቸው ከህግ ውጪ በግለሰቦች ከተወሰደባቸው መካከል 38 ሴቶች፣ አረጋውያንና አካል ጉዳተኞች 15 ሄክታር የእርሻ መሬት በፍርድ ቤት ክርክር ተወስኖ እንዲመለስላቸው ተደርጓል፡፡ ሌሎች የ12 ግለሰቦች የመሬት ይዞታ አቤቱታ ሰነድ ተጣርቶ ለወረዳው የፍትህ አካል ለውሳኔ መላኩን ቡድን መሪው አስታውቀዋል፡፡ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም መምሪያ የመሬት አስተዳደር ቡድን መሪ አቶ ወልደማርቆስ መኩሪያ በዘንድሮ ዓመት በዞኑ 13 ወረዳዎች 242 ግለሰቦች ከህግ አግባብ ውጪ የተወሰደባቸውን 114 ሄክታር መሬት ማስመለስ መቻሉን ገልጸዋል። የእርሻ መሬታቸው እንዲመለስላቸው ከተደረጉ የሕብረተሰብ ክፍሎች መካከልም 175 አካል ጉዳተኞች፣ 15 አረጋዊያንና 52 ሴቶችና ህጻናት መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ መምሪያው መሬታቸው ለተመለሰላቸው የህብረተሰብ ክፍሎችም አዲስ የመሬት ባለቤትነት ይዞታ ማረጋገጫ ደብተር ተዘጋጅቶ እንዲሰጣቸው ማድረጉን ተናግረዋል፡፡ መሬቱን አላግባብ ይዘው ሲጠቀሙ የነበሩ 172 ግለሰቦችም በተጭበረበረ መንገድ ያወጡት የመሬት ባለቤትነት የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር ተሰርዞ በህግ ክስ እንዲመሰረትባቸው መደረጉንም ቡድን መሪው አስታውቀዋል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም