“ውስጠ ወይራ፤ ድብቅ ሴራ ያዘለ…” በህዳሴ ግድብ

185
እንግዳው ከፍያለው /ኢዜአ/ የጠራ ሰማይ መስሎ የተዘረጋው የጣና ሃይቅ በቀኑ ጸሃይ ማብረቅረቅ ጀምሯል። በክረምቱ ደለል የደፈረሰ ገጽታው እየተመለሰ መሆኑን የሃይቁ ውሃ እየጠቆረ መምጣት ያሳብቃል። ሰዓቱ አምስት ተኩል አካባቢ በመሆኑ ከውሃው ነጸብረቅ ውጭ የሚረብሽ ሞገድም ሆነ ሌላ ድምጽ አይስተዋልም። ጸጥ ረጭ ብሏል። ትክ ብለው ሲያዩትም የማንጸባረቅና የመፍለቅለቅ ምልክት የሚታይበት ነው።አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ቀለም ያለውን ሰንደቅ ዓላማችን የሚያውለበልቡ ጀልባዎች ከወዲያ ወዲህ ሲራወጡ ይታያሉ። ጣና ሃይቅን ደግሜ ደጋግሜ ትክ ብዬ አየሁት። 90 ኪሎ ሜትር በላይ ከባህርዳር እስከ ጎርጎራ ጎንደር የተዘረጋውን የውሃ ላይ ጉዞ በህሊናዬ ቃኘሁት። በውስጡ የሚኖሩ ዓሳዎችን፣ ጉማሬዎችን፣ አእዋፋትንና ሌሎች ነፍሳትን በአይነ ህሊናዬ ጎበኘሁ። ምንም እንኳ ሰዓቱ የቀኑ አጋማሽ ላይ ቢሆንም ከሃይቁ በሚመጣው ነፋስ የአካባቢውን ሙቀት ወደ ቅዝቃዜ ስለቀየረው ምቾት ተሰምቶኛል። የጣና ሃይቅን ሳስብ ከሱ በሶስት እጥፍ ውሃ ይይዛል ተብሎ የሚነገርለትን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በዓይነ ህሊናዬ ማማተር ጀመርኩ። ግድቡ በትልቅነቱ በአፍሪካ የመጀመሪያ በዓለም ደግሞ ሰባተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተነግሯል። ግድቡ 145 ሜትር ከፍታና 1 ሺህ 870 ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን 74 ቢሊዮን ኪዩብክ ሜትር ውሃ እንደሚይዝ  መረጃዎች ያመለክታሉ። ውሃው በዋናው ግድብ ሲያዝ ዝቅተኛ በሆነው በግድቡ በቀኝ አቅጣጫ ውሃው እንዳይፈስ የሚያደርግ 5  ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው በአለት ድንጋይ ተጠቅጥቆና በአርማታ የሚሞላ ሳድል ዳም ተጨማሪ ግድብን በማካተት እየተገነባ የሚገኝ ነው። ግድቡ ሲሞላም ውሃው 246 ኪሎ ሜትር ወደ ኋላ በመመለስ እንደሚሞላና ለቱሪዝም፣ ለዓሳ ልማትና ሌሎች አገልግሎቶች እንደሚውል መረጃዎች ያመለክታሉ። አባይ የአገር ሲሳይ ለመሆን ተቃርቧል እየተባለ የሚነገረውም ለዚሁ ነው። የህዳሴ ግድብ ግንባታ 65 በመቶ ለሚሆነው የኤሌክትሪክ ሃይል ተጠቃሚ ያልሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ የተስፋ ጭላንጭል ነው። የማታውን ጨለማ በብርሃን ለመተካት በተስፋ እየተጠባበቀ የሚገኘውም ለዚህ ነው ። በእንጨት ማገዶና በኩራዝ መብራት ለትራኮማና ሌሎች የዓይን በሽታ የተጋለጡ እናቶች የህዳሴውን ግድብ መጠናቀቅ እንደ ተአምር እንደሚጠብቁትም የአደባባይ ሚስጥር ነው። ስድስት ሺህ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሃይል ያመነጫል መባሉ የሚታወስ ነው። ይህም ለአገራችን ህዝቦች ብቻ ሳይሆን ዓመቱን ሙሉ የሚመነጨው የኤሌክትሪክ ሃይል ለሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኬንያ፣ ጅቡቲ፣ ኤርትራና ግብጽ ጭምር በመጠነኛ ዋጋ ሃይል እንዲያገኙ የሚያስችል ነው ተብሎ ተስፋ የተጣለበት ፕሮጀክት ነው። የምስራቅ አፍሪካን በሃይል ልማት በማስተሳሰር ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ግንኙነታቸውን በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ለማጠናከር ያስችላል ተብሎ የሚጠበቅ ግዙፍ ፕሮጀክት መሆኑን ብዙዎች ሲተነትኑ ሰምተናል። የጣና ሃይቅ ግርማ ሞገስን ከህዳሴው ግድብ ጋር ያነጻጸርኩት በሹም አቦ መናፈሻ አልፌ ከእግረኛ መንገዱ ስር ካለው ወደብ ላይ በመሆን ነው። ባህርዳር የመጣ እንግዳ ከአልማ ዋናው መስሪ ቤት ወደ ሰሜን አቅጣጫ እስከ ክልሉ እንግዳ መቀበያ ድረስ በከተማውና በሃይቁ መካከል የእግረኛ መንገድ አለ። ሁለተኛው ደግሞ ከማንጎ መናፈሻ፣ በድሮው ግዮን ሆቴል፣ ኩሪፍቱና ህዳር 11 መናፈሻ ጀርባ ያለው የእግር መንገድ ነው። እንግዶች በእግራቸው በመጓዝ ሃይቁን እንዲጎበኙ ታስቦ የተገነባ በመሆኑ ዘወትር ከሰዓት በኋላ ከሰው መብዛት የተነሳ በከተማው የቀረ ሰው ያለ አይመስልም። የጣናን ንጹህ አየር ለመቀበል ሁሉም ይተራመሳል። በሹም አቦ አልፌ የቆምኩበት ወደብ የውጭና የአገር ውስጥ ጎብኚዎችን የሚያንሻረሽሩ ጀልባዎች ማረፊያ፣ የጎብኚዎች መሳፈሪያ ሆኖ እያገለገለ እንደሚገኝ በገመድ ተጠልፈው የእንግዶችን መምጣት የሚጠባበቁት ጀልባዎች ይመሰክራሉ። እንግዶችን ተቀብለው የሚያስተናግዱ ወጣቶችም እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ። የባህርዳር ዩንቨርሲቲ የሲቪልና የውሃ ምህንድስና ሁለት ምሁራን አብረውኝ አሉ። ከእነሱ ጋር የተገናኘንበት ዋና ጉዳይ ሰሞኑን በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የተመራው ተደራዳሪ ቡድን በኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሊት ዙሪያ ከግብጽና ከሱዳን ጋር በደረሱባቸው ስምምነቶች ዙሪያ ቃለ መጠይቅ ለማድረግ ነው። የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ግንባታው ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት እልህ አስጨራሽ ድርድር ከግብጽና ከሱዳን ጋር መካሄዱ ይታወቃል። “ማን ይናገር የነበረ ማን ያርዳ የቀበረ” እንደሚባለው ምሁራኑ በድርድሩ ሂደትና አሁን በተደረሰበት ጉዳይ ላይ እንደሚከተለው ማብራሪያ ሰጥተዋል። በዩኒቨርሲቲው የሲቪልና ውሃ ምህንድስና ፋካልቲ መምህርና ተመራማሪ ዶክተር አሰግደው ጋሻው እንዳሉት ታላቁ የኢትዮጵያ ህደሴ ግድብ ለቀጠናዊ ትስስርና ለጋራ ኢኮኖሚያዊ ብልጽግና ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው ቢሆንም ግብጾች በዚህ መልኩ አያዩትም በማለት ንግግራቸውን ጀመሩ። ግብጽ የምታነሳው የድርድር ሃሳብ ምን ነበር? ውስጠ ወይራ የሚያሰኘውስ? የሚል ጥያቄ አነሳሁ። ምን መሰለህ በማለት መልሳቸውን ጀምሩ። የግብጽ ተደራዳሪዎች የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በማስፈራራትም ሆነ ባገኙት አጋጣሚ ማስቆም ነበር የመጀመሪያ ግባቸው። ይህ ብቻ አይደለም ከዚህ በኋላ ሌላ ግድብም ሆነ ልማት በአባይ ወንዝ ላይ እንዳናካሔድ የሚያደርጉ ሃረጎችንና አረፍተ ነገሮችን በማስገባት ያመጣሉ። ሴራው በዚህ ብቻ የሚቆምም እንዳይመስልህ እኛ የምንደራደረው ስለ ህዳሴ ግድብ መሆኑን እያወቁ ጉዳዩን ከአስዋን ግድብ ጋር ያያይዙታል። የአስዋን ግድብ ከሚይዘው ውሃ እንዳይቀንስ በሚል አጀንዳ ይዘው ይመጣሉ። የአስዋን ግድብ እንደሚታወቀው የግብጽ ግድብ ነው። እኛ በማንቆጣጠረውና በማይመለከተን ጉዳይ ከህዳሴው ግድብ ለማያያዝ የሚሞክሩት ዞሮ ዞሮ የኢትዮጵያን በአባይ ውሃ የመጠቀም መብት ለመገደብ ከማሰብ የሚመነጭ እኩይ ተግባር ነው። ሁልጊዜም የግብጽ ተደራዳሪዎች የመደራደሪያ ሃሳብ “ማኖ”  ለማስነካት ነው የሚመጡት። የኢትዮጵያ ተደራዳሪዎች በምን ስልት ነው የግብጽን የውስጠ ወይራ የድርድር ሃሳብ የሚያከሽፉት? ሌላ ጥያቄ ተከተለ። የኛ ተደራዳሪዎች ሁልጊዜም አቋማቸውና መርሃቸው የሚካሄደው ድርድር በህዳሴ ግድብ ብቻ እንዲመሰረት ለማድረግ ነው የሚደራደሩት። በቀጣይ የሚገነቡ ግድቦችና ሌሎች ልማቶችንም በምንም መልኩ እንዳይነካና የአስዋን ግድብ የራሳቸው ጉዳይ እንጂ እኛን እንደማይመለከት በማሳየት የአገራችንን ጥቅም ለማስጠበቅ በቁርጠኝነት የሚያካሂዱት ድርድር እልህ አስጨራሽ ነበር ይላሉ። ለዚህም የኢትዮጵያ ተደራዳሪዎች የዓለም አቀፍ የውሃ አጠቃቀም መርሆዎችን መሰረት በማድረግ ግድቡ የታችኛውን የተፋሰስ አገራት ላይ የጎላ ጉዳት እንደማያደርስና ተባብረው ከሰሩ ደግሞ ለቀጠናው ኢኮኖሚያዊ እድገት ያለውን ፋይዳ በማሳየት ነበር መርህን ጨብጠው የሚከራከሩት። አሁን ላይ ድርድሩ እየበሰለና ፍሬ እያፈራ ሲመጣ የነበረው የጦርነት ነጋሪት ጉሰማ፣ ዛቻና ማስፈራራት በአንጻሩ እየቀነሰ መምጣቱን መገንዘብ ይቻላል። ይህም የብዙ ውጣ ውረድ ውጤት እንጂ ዝም ብሎ የተገኘ ድል አይደለም ባይ ናቸው። "ባለፈው ሳምንት በአሜሪካ የተካሄደው ድርድርና ስምምነት የተደረሰባቸው ጉዳዮችም ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ በፍትሃዊነት የመጠቀም መብቷን ያስከበረ በመሆኑ በተደራዳሪዎቻችን እንድንኮራና በሙሉ ልብ እንድንደግፋቸው የሚያደርግ ውጤት የተገኘበት መሆኑን መገንዘብ ይቻላል" ያሉት ወደ እኔ ትክ ብለው እያዩ ነበር። ለዚህም በጊዜ ሂደት የኢትዮጵያ ተደራዳሪዎች ልምዳቸው እያደገ፣ ህዝባዊነታቸው እየጨመረና ለአገር ሉአላዊነት መከበር ያላቸው ቁርጠኝነት እየጎለበተ በመምጣቱ ከተገኘው ውጤት በላይ ምስክር አያሻም በማለት ያሰምሩበታል። የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከባህር ጠለል በላይ 595 ሜትር በውሃ እንዲሞላ ስምምነት መድረሱ ለብዙ ሰዎች ሃሳቡ ግልጽ አልሆነም፤ ምን ማለት ነው? ሌላ ጥያቄ አቀረብኩ። “ የግድቡ መሰረት የተቀመጠው ከባህር ጠለል በላይ 500 ሜትር ላይ መሆኑ ይታወቃል አሉ ፊታቸውን ወደ ጣና ሃይቅ እያዞሩ። በአሁኑ ስምምነት ከመሰረቱ በላይ 95 ሜትር ተፋጥኖ እንዲሞላ የሚፈቅድ ነው። በዚህ የግድቡ ከፍታ ላይ 18 ነጥብ 3 ቢሊየን ሜትር ኩብ ውሃ ይይዛል። ወደ ሃይል ማመንጫ ተርቫይኖቹ ውሃ የሚያልፍበት በር የሚገኘውም በዚህ ከፍታ ላይ ነው። ውሃው በዚህ ልክ ከተሞላ በበሮቹ እያለፈ ሃይል ማመንጨት እንችላለን ማለት ነው። ከዚህ በላይ ያለው የውሃ መውጫ የሌለው የተደፈነ ግድብ አካል ነው። መጠባበቂያ ውሃው በክረምት እየተሞላ በበጋው ወቅት ሃይል ለማመንጨት የሚውል ነው። በዚህ ከፍታ ልክ ውሃው ከሞላ ወደ ሱዳንም ሆነ ግብጽ የሚለቀቀው ውሃ ሃይል እያመነጨ የሚፈስ ነው የሚሆነው። በቅርቡ የሃይል ማመንጫ ተርቫይኖች እንደሚቀነሱ የሚነሳውን ጥያቄስ እንዴት ያዩታል? “ይሄ የሳይንስ ጉዳይ ነው። ዋናው ግድቡ የሚይዘው ውሃ ዓመቱን ሙሉ ምን ያህል ኤሌክትሪክ ሃይል ያመነጫል የሚለው ነው። ከተርባይኑ ጋር የሚያያዝ አይደለም”። እንዴት? ሌላ ጥያቄ ቀጠለ። “ግድቡ የሚይዘው ውሃ 74 ቢሊየን ሜትር ኩብ መሆኑ ይታወቃል። ሁሉንም ተርቫይኖች በማንቀሳቀስ ላመንጭ ካልክ ውሃውን በሶስት ወራት ውስጥ ጨርሰህ ቁጭ ማለት ነው የሚገጥመህ እድል። ለዛ ነው የተወሰኑ ተርቫይኖችን በማንቀሳቀስ ዓመቱን ሙሉ ሃይል ማግኘት አዋጭ ነው እየተባለ የሚገለጸው”። አሞላሉ ላይ ከሃምሌ እሰከ ነሃሴ እንደ ሁኔታው እስከ መስከረም የተባለውስ እንዴት ይታያል? በክረምት ወቅት የሚፈሰው የአባይ ውሃ 70 በመቶውን የሚሸፍን መሆኑ በተደጋጋሚ በተካሄዱ ጥናቶች ተረጋግጧል። ያ ማለት ወቅቱ ከሃምሌ እስከ መስከረም አካባቢ ማለት ነው። በቀሪ ዘጠኝ ወራት የሚፈሰው ውሃ ተደምሮ 30 በመቶ ብቻ ነው። ምክንያቱም በበጋው ወቅት የዓባይ ወንዝ ፍሰት በእጅጉ የሚቀንስ መሆኑን ነው። በክረምቱ የሚፈሰውን ውሃ መያዝ ከቻልን ግድቡን ለመሙላት የሚያስቸግር አይደለም። ምክንያቱም በቀሪ ወራት የሚመነጨው ውሃ ሃይል እያመነጨ የሚያልፍ መሆኑ ስለሚታወቅ። ሁሉጊዜም ሃይል ማመንጨት ከጀመረ በኋላ ሃይል ሳያመነጭ የሚያልፍ ውሃ ስለሌለ ብዙ ለቀቅንም፤ ትንሽ ለቀቅንም ከራሳችን ጥቅም ጋር የሚያያዝ ነው። እውነታው ግድቡ ዓመታዊ ፍሰቱ የተመጣጣነ ውሃ ግብጽና ሱዳን እንዲያገኙ ያስችላታል። በረሃ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አስዋን ግድብ ላይ ከፍተኛ የውሃ ትነት አለ። በሱዳንም እንዲሁ። አሁን ግን ውሃውን ዝቅተኛ ትነት ባለበት በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ይዞ የተመጣጠነ ውሃ ዓመቱን ሙሉ ይለቀቃል ማለት ነው። ሱዳን ደግሞ በክረምት ወቅት በደለልና በጎርፍ መጥለቅለቅ ሲደርስ የነበረው ጉዳት ይቀንስላታል። በባህርዳር ዩንቨርሲቲ የመስኖ ምህንድስና አስተባባሪ የሆኑት ዶክተር ዳኝነት ስልጣን በበኩላቸው "በድርቅና በተራዘመ ድርቅ የተባለው የስምምነት አካል ጥንቃቄን የሚጠይቅ ነው" በማለት ማብራራታቸውን ይቀጥላሉ። ድርቅ በኢትዮጵያ፣ በሱዳንና በግብጽ የሚታይበት መንገድ ላይ መግባባት መኖር አለበት። በኛ ሃገር የተራዘመ ድርቅ የሚባለው በ1977 ዓ.ም አጋጥሞን እንደነበረው ዓይነት ነው። እንደሚታወቀው ከናይል ውሃ 85 በመቶ የሚሆነው የሚገኘው ከኢትዮጵያ ከሚሄደው የጥቁር አባይ ወንዝ ነው። ይሄን ያህል ድርሻ ያላት አገራችን በአካባቢው በሚካሄደው ልማት ቀላል የማይባል ተጽእኖ በአሉታዊም ሆነ በአዎንታዊ ማሳረፍ  የምትችል ናት። ድርቅ ከመጣ ደግሞ አሉታዊ ተጽእኖው በዛው ልክ እየጨመረ መሄዱ አይቀርም። የድርቅ አሉታዊ ተጽእኖን ለመቀነስ "አገራችን የተጀመረውን የተፈጥሮ ሃብት ማልማትና መንከባከብ ስራ አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል የሚል እምነት አለኝ" ብለዋል። ለአፈርና ውሃ እቀባ ስራውም በእውቀት፣ ገንዘብ፣ በመስሪያ ቁሳቁስና ሌሎች ድጋፎች ሱዳንና ግብጽ መሳተፍ አለባቸው። ሌሎች አማራጮችም መታየት ያለባቸው ደግሞ የጂኦተርማል፣ የጸሃይና የነፋስ ሃይል ልማትን ማስፋፋት ይገባል። ይህም ለገጠሩ ማህበረሰብ በቀላሉ ሃይልን ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል ነው። ውሃን በቁጠባ መጠቀም ይገባል። ሱዳንም ሆነች ግብጽ የዓለም የአየር ንብረት ተለዋዋጭ በሆነበት በዚህ ዘመን የውሃ አጠቃቀማቸውን በቁጠባ ማድረግ አለባቸው። አገራችን እስከ አሁን በአባይ ወንዝ ላይ የተጠቀመችበት ጊዜ ባይኖርም ለወደፊት ውሃን በቁጠባ መጠቀም መለመድ ያለበት ጉዳይ ነው ብለዋል። ከላይ ለተጠቀሱት ጉዳዮች ሁሉ ሶስቱ አገራት በትብብር መስራት እንዳለባቸውም ምሁራኑ ምክረ ሃሳባቸውን ለግሰዋል። የግብጽን ተለዋዋጭና መጨበጫ የሌለው የማደናገሪያ የድርድር ሃሳብ በማምከን በኩል የእኛ ተደራዳሪዎች ያበረከቱት አስተዋጽኦ በትውልድ ዘንድ ሲዘከር የሚኖር ነው። በዚህም ግብጽ እስከ 21 ዓመት ለማራዘም ያቀረበችው የድርድር ሃሳብ ውድቅ ሆኖ የኢትዮጵያ ተደራዳሪዎች ባቀረቡት ከአራት እስከ ሰባት የሚለው ተቀባይነት ማግኘቱ ማረጋገጫ ነው ብለዋል። በቀጣይ የስምምነቱ መጨረሻ ምእራፍ ይደርሳል ተብሎ በሚታሰበው የዋሽንግተን ድርድር ይሄን ስማቸውን የሚያስጠብቅ ስራ ሰርተው ይመጣሉ የሚል እምነት እንዳላቸው ምሁራኑ ተናግረዋል።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም