በትግራይ ከ1 ሚሊዮን በላይ ጎልማሶችን ለማስተማር ታቅዷል

56

መቀሌ ኢዜአ ጥር 19/12 ዓ/ም በትግራይ ክልል ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች ተጠቃሚ የሚያደርግ የተቀናጀ ተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርት መሰጠት መጀመሩን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ባህታ ወልደሚካኤል እንደገለፁት የተቀናጀ ተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርት በዚህ ወር የተጀመረው በክልሉ በሚገኙ 15 ወረዳዎች ላይ ሲሆን በሒደት 43 ወረዳዎችን ተደራሽ የሚያደርግ  ነው ።

በፕሮግራሙ የመጀመሪያው ምእራፍ 15 ሺህ 533 ሴቶችን ጨምሮ ከ27 ሺህ 700 በላይ ጎልማሶች ትምህርቱን በመከታተል ላይ ናቸው ።

የጎልማሶች ትምህርት ፕሮግራሙ ግብርና፣ ጤና፣ መልካም አስተዳደር፣ ፀጥታ እና ሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች ያካተተ መሆኑን የቢሮው ምክትል ኃላፊ ተናግረዋል ።

ፕሮግራሙን ለማሳካት 500  ሙያተኞች ተመድበው የመማር ማስተማር ስራውን እያካሄዱ እንደሚገኙ ነው የተገለፀው ።

የተግባር ተኮር የመማር ማስተማር ስራው የሚካሄደው ጎልማሶቹን ከልማት ስራቸው በማያስተጓጉል መልኩ ቅዳሜና እሁድ ላይ ነው ።

ጎልማሶቹ በሳምንት አንድ ሰዓት እየተማሩ በ216 ሰዓታት ውስጥ የሚጠበቅባቸውን የመፃፍ፤ማንበብና የሂሳብ ማስላት ችሎታና ክህሎት እንዲይዙ ይደረጋል ብለዋል።

ተግባር ተኮር የትምህርት ፕሮግራሙ የግብርናና ገጠር ልማት ሥራዎችን በዘመናዊ መንገድ ለማከናወን እንዲያግዝ ተደርጎ የተቃኘ መሆኑንም አቶ ባህታ ገልጸዋል።

የተግባር ተኮር የትምህርት ፕሮግራሙ አንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ጎልማሶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑንም ከምክትል ቢሮ ኃላፊው ገለፃ ለማወቅ ተችሏል ።

የጎልማሶች ትምህርት በመከታተል ላይ ከሚገኙ ጎልማሶች መካከል የዓዲግራት ከተማ ነዋሪ አቶ ገብረክርስቶስ ሙሉ በሰጡት አስተያየት ከፕሮግራሙ የመጻፍና የማንበብ እውቀት እንደሚቀስሙ ተስፋ አሳድረዋል ።

''ማንኛውም ስራ ስኬታማ የሚሆነው በትምህርት ሲታገዝ ነው ያሉት አቶ ገብረክርስቶስ እየተሰጠን ያለው ትምህርት በአግባቡ ለመከታተልና ሌሎችም ትምህርቱን እንዲከታተሉ ለመምከር ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በትግራይ ምስራቃዊ ዞን በክልተ አውላዕሎ ወረዳ የአይናለም ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ንጉሰ አስመላሽ በበኩላቸው የጎልማሶች ተግባር ተኮር ትምህርቱ  ዘመናዊ አሰራርን የሚያበረታታ  በመሆኑን ጉጉት እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም