አገሪቷ የትምህርት ሽፋንን ብታሟላም የጥራት ችግር አጋጥሟታል - ጥናት

91
አዲስ አበባ ጥር 19/ 2012 በኢትዮጵያ የትምህርት ሽፋን ቢሟላም ጥራቱ በሚፈለገው ደረጃ ላይ እንዳልሆነ የአንድ ዓለም አቀፍ የአጥኚዎች ቡድን ጥናት አመላከተ። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንትና የጥናቱ አስተባባሪ ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና የትምህርት ሽፉኑ በሚፈለገው ደረጃ ቢሆንም ጥራቱ ላይ ግን ችግር ገጥሞናል ብለዋል። ዩኒቨርሲቲው ራይስ ከተሰኘ ዓለም አቀፍ የአጥኚዎች ቡድን ጋር ያካሄደው ጥናት የአገሪቷ የትምህርት ጥራት ዝቅተኛ መሆኑን በመግለጽ በተለይም የሴቶች ትምህርት ማቋረጥ ሊታሰብበት ይገባል ብሏል። ለትምህርት ጥራቱ ማሽቆልቆል የሃሰት ሪፖርት፣ የእርዳታ ድርጅቶች በትምህርት ስርዓቱ ላይ ጣልቃገብነትና የሚወርዱ መመሪያዎችን በተዛባ መንገድ መረዳት ምክንያቶች ሆነው ቀርበዋል። ለትምህርት ቤቶች ውጤት ተኮር በጀት መመደቡም ተማሪዎች ላይ ለውጥ ሳይመጣ 'ተማሪዎች በቅተዋል የሚል የሃሰት ሪፖርት መረጃ እንዲያቀርቡ ማድረጉም ተጠቅሷል። ለሴት ተማሪዎች ትምህርት ማቋረጥ ደግሞ ምቹ የመጸዳጃ ቤት አለመኖር እንደ ምክንያት ቀርቧል። ፕሮፌሰር ጣሰው ጥናቱ እንዳመላከተን የትምህርት ስርዓቱ የሰራና ያልሰራን የሚመዝን አደረጃጀት የለውም ሲሉ ተናግረዋል። በመሆኑም ይህ ጥናት ወደ ችግሩ መፍትሄ ለመግባት ትልቅ መነሻ ሆኖናል ብለዋል። የትምህርት ሚንስትር ዴኤታዋ ወይዘሮ ጽዮን ተክሉ በበኩላቸው ጥናቱ ለአዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ትልቅ ግብዓት ይጨምርልናል ነው ያሉት። ጥናቱ የመማር ማስተማሩን ክፍተቶች የሚጠቁም በመሆኑ ፋይዳው ከፍ ያለ እንደሆነ ገልጸዋል። በአገሪቷ የሚስተዋለውን የትምህርት ጥራት ማሽቆልቆል ለማረምና ችግሩን ከምንጩ ለመለየት በጥናቱ ሰፊ ስራ እንደተሰራም ነው ያብራሩት። በጥናቱ የተገኘውን ውጤት ይዘን ሊስተካከሉ የሚገባቸውን በርካታ አሰራሮች እናስተካክላለንም ብለዋል ሚኒስትር ዴኤታዋ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም