በክልሉ የመንግስት ገንዘብ አጠቃቀምና ግብር አሰባሰብ ላይ ክፍተት እንዳለ ተገለጸ

51
መቀሌ ኢዜአ ጥር 19/12፡- በትግራይ ክልል የመንግስት ተቋማት ውስጥ የገንዘብ አጠቃቀምና የግብር አሰባሳብ ላይ ክፍተት እንዳለ የክልሉ ዋና ኢዲተር አስታወቀ፡፡ ዋና ኦዲተር ዶክተር ረዳኢ በርሀ በመቀሌ እየተካሄደ ባለው የክልሉ ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ ላይ ባቀረቡት ሪፖርት እንዳሉት በ27 ተቋማት አለአግባብ የተከፈለ 27 ሚሊዮን 600ሺህ ብር እንደተገኘ በሂሳብ ምርመራ ተረጋግጧል። ባልተማላ ማስረጃ ደግሞ በክልሉ 17 ተቋማት 47 ሚሊዮን ብር ክፍያ ተፈጽሞ መገኘቱን አስታውቀዋል። በተለያዩ ተቋማት መመሪያን ያልተከተለ ከ19 ሚሊዮን ብር በላይ ግዥ ተፈጽሞ መገኘቱም ተመልክቷል። ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ከተለያዩ የግብር ምንጮች በወቅቱ ለመንግስት ገቢ መሆን የነበረበት 36 ሚሊዮን 800ሺህ ብር እንዳልተሰበሰብ በሂሳብ ምርመራ ማረጋገጣቸውን ዶክተር ረዳኢ ገልጸዋል። ምርመራ ከተደረገባቸው አብዛኛዎቹ ተቋማት መካከል በበጀት ዓመቱ ሂሳባቸውን የማይዘጉና አንዳንዶቹም እስከ አስር ዓመታት ሲንከባለል የመጣ ግኝት ያለባቸው መሆኑን ዋና ኦዲተሩ አስረድተዋል። “የተቋማቱ ዋነኛ ችግር ስራውን እንዲመሩ የተቀመጡት የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ለፋይናንሱ ዘርፍ ተገቢውን ቁጥጥርና ክትትል በማድረግ ተጠያቂነትን የሚያስከትል አሰራር ባለመከተላቸው ነው” ብለዋል። የኦዲት ግኝቱ መነሻ በማድረግ የተለያዩ የቢሮ ኃላፊዎች ምላሽ የሰጡ ሲሆን፣ የምክር ቤቱ አባላትም በጉዳዩ ዙሪያ ተወያይተዋል። አብዛኛዎቹ የቢሮ ኃላፊዎች ግኝቱ ከመሾሟቸው በፊት የተፈጸመ እንደሆነ ሲገልጹ አንዳንዶቹ ደግሞ ከውጭ የሚገዙ እቃዎች ቅድመ ክፍያ መፈጸም ጨምሮ በሂደት ላይ ያሉ መሆናቸውን ለምክር ቤቱ አስረድተዋል። የኦዲት ግኝቱ በግለሰብ ሳይሆን በተቋም ደረጃ መሆኑን እንደሚያሳይ የገለጹት ደግሞ በክልሉ ምክር ቤት የበጀትና ኦዲት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ንጉሰ ለገሰ ናቸው። የስራ ኃላፊዎች በየተቋሞቻቸው ያሉትን ችግሮች መፍታት ሲገባቸው ''ከኛ በፊት'' የተፈፀመ ነው የሚለውን ምክንያት አግባብነት እንደሌለውም አስረድተዋል። የመንግስትና የህዝብ ገንዘብ በወቅቱ ሰብስቦ ለታለመለት ዓላማ እንዲውል የተቋማት ተጠሪዎች ኃላፊነታቸው በተገቢው ሊወጡ እንደሚገባም አሳስበዋል። ከምክር ቤቱ አባላት መካከል ወይዘሮ ቅዱሳን ነጋ አብዛኛዎቹ የስራ ኃላፊዎች የመንግስትን ስራ በመከታተል በኩል ክፍተት እንዳለባቸው ገልጸዋል። የመንግስትና የህዝብ ሃብት የሚያባክን ኃላፊ ተጠያቂ ሊሆን እንደሚገባም ያመለከቱት ደግሞ ሌላው የምክር ቤቱ አባል አቶ ገብረ ካሕሳይ ናቸው። የክልሉ ዋና ኦዲተር ሪፖርት የምክር ቤቱ አባላት ካጸደቁት በኋላ የክልሉ ስራ አስፈፃሚ ተገቢውን ክትትል እንዲያደርግና በተቋማቱ ስለሚወሰዱ እርምጃዎች የሚገልፅ ራሱን የቻለ ሪፖርት በበጀት ዓመቱ መጨረሻ እንዲቀርብም ወስነዋል። የምክር ቤቱ አባላት በሌሎች አጀንዳዎች ዙሪያ ውይይታቸውን ቀጥለው እንዳሉ ሪፖርተራችን ከስፍራው ዘግቧል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም