የመዲናዋ ሆቴሎች ለአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ አስፈላጊውን ዝግጅት አደረጉ

125
ጥር 19 ቀን 2012 ( ኤዜአ) በአዲስ አበባ ታላላቅ ሆቴሎች ለ33ኛው የአፍሪካ ኀብረት የመሪዎች ጉባኤ የሚመጡ እንግዶችን ለመቀበል አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጋቸውን ገለጹ። የኀብረቱ 33ኛው የመሪዎች ጉባዔ ከጥር 28 እስከ የካቲት 2 ቀን 2012 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል። በጉባዔ ላይ የአባል አገራቱ መሪዎች፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፣ ዲፕሎማቶችና የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች ይሳተፋሉ። ዘንድሮ የሚካሄደውን ጉባዔ አስመልክቶ ኢዜአ በአዲስ አበባ ከሚገኙ ታላላቅ ሆቴሎች መካከል ሦስቱን ቃኝቷል። የኢሊሌ ኢንተርናሽናል፣ የራዲሰን ብሉ እና የኢንተርኮንቲኔንታል አዲስ ሆቴሎች ለኀብረቱ ጉባዔ የሚመጡ እንግዶችን ለመቀበል አስፈላጊውን ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን ገልጸዋል። በጉባዔው የሚሳተፉ እንግዶች የኢትዮጵያን እንግዳ ተቀባይነት በትክክል ተገንዝበውና በአገልግሎቱም ረክተው ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ለማድረግ አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን የሆቴሎቹ የስራ ኃላፊዎች ገልጸዋል። በጉባዔው ላይ የአባል አገራቱ መሪዎችና ሌሎች ታላላቅ ሰዎች የሚገኙ በመሆኑ የሚመጥናቸውን መስተንግዶ ለማድርግ ተዘጋጅተናል ብለዋል። እንግዶቹን ከቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ በመቀበል እንዲሁም በቆይታቸው ደህንነታቸው እንዲጠበቅ ከወረዳ፣ ከክፍለ ከተማና ከአካባቢው የፖሊስ አባላት ጋር በቅንጅት ለመስራት ተዘጋጅተናልም ነው ያሉት። ከጉባዔው ውጪ በሚኖራቸው ጊዜም የተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎችን የማስጎብኘትና የኢትዮጵያን ባህል እንዲያውቁ የማድረግ ስራ እንደሚሰሩም ጠቁመዋል። ይህም ለሆቴል ኢንዱስትሪው ከሚያበረክተው አስተዋጽኦ ባሻገር የአገርን ገጽታ ለመገንባትና የውጭ ምንዛሬ ለማስገኘት ትልቅ ድርሻ እንደሚኖረውም አክለዋል። የዘንድሮ 33ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ “የጥይት ድምጽ የማይሰማባትን አህጉር እውን በማድረግ ለአፍሪካ ልማት ምቹ ሁኔታ እንፍጠር” በሚል መሪ ሃሳብ ይካሄዳል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም