አሜሪካ በኢትዮጵያ ለከፈተቻቸው የትምህርት አገልግሎት ማዕከላት ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ አውጥታለች

67
ጥር 19/2012 ( ኢዜአ) አሜሪካ ኢትዮጵያ ውስጥ ለከፈተቻቸውና ለትምህርት አገልግሎት የሚውሉ ስድስት ማዕከላት ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ማድረጓን አስታወቀች። ማዕከላቱ አሜሪካ በትምህርት መስክ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር ያላትን ቁርጠኝነት ማሳያዎች ናቸው ተብሏል። የአሜሪካ አፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ቲቦር ናጊ በኢትዮጵያ ያደረጉትን ጉብኝት አጠናቀዋል። ሚኒስትሩ በጉብኝታቸው በመቐለ ዩኒቨርሲቲ አዲ-ሀቂ ካምፓስ ለትምህርት አገልግሎት የሚውለውን ማዕከል /አሜሪካን ኮርነር/ መመረቃቸው ይታወቃል። ማዕከሉ ለትምህርት እንዲሁም ለጥናትና ምርምር ተግባራት የሚውል ሲሆን ወጣት መሪዎችን ማብቃትና ማልማት ላይ ዓላማ ማድረጉን በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል። በመቐለ ዩኒቨርሲቲ የተከፈተው ማዕከል ዲጂታል ቤተ መጻህፍት ቤት ያለው ሲሆን የተለያዩ እትሞች፣ አሜሪካን የተመለከቱ ጉዳዮች ላይ የታተሙ ጽሁፎች፣ መጽሐፎችና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን መያዙ ተመልክቷል። በኮምፒዩተሮች ላይ የተገጠሙት ቴክኖሎጂዎች ለፈጠራ አገልግሎት ጉልህ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋልም ተብሏል። ቲቦር ናጊ የአሜሪካ ማዕከል ሀሳቦችን በነጻ ለመለዋወጥ የሚያግዙ፣ በሚንሸራሸሩ ሀሳቦች አዳዲስ ክህሎቶች እንዲገኙና እንዲበልጽጉ እንደሚያደርግ ተናግረዋል። በማዕከሉ የሚገኙ ቴክኖሎጂዎች ተማሪዎች ከአሜሪካና ከተቀረው ዓለም ጋር የቀረበ ትስስር እንዲኖራቸው ያደርጋሉ ብለዋል። በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ መቐለ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ በኢትዮጵያ ለከፈታቸው ስድስት የአሜሪካ ማዕከላት ከ2 ሚሊዮን 170 ሺህ ብር ላይ ወጪ ማድረጉን መግለጫው ጠቅሷል። አምስቱ ማዕከላት በባህርዳር፣ በጅማና ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲዎች፣ በአዲስ አበባ በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተመጻህፍትና ቤተመዛግብት ኤጀንሲ ይገኛሉ። ማዕከላቱ አሜሪካ በትምህርት መስክ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር ያላትን ቁርጠኝነት ማሳያዎች ናቸው ሲል ነው የኤምባሲው መግለጫ ያመለከተው። ቲቦር ናጊ በመቐለ ዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው አሜሪካ በኢትዮጵያ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እየተገበረቻቸው ባሉ መርሃ ግብሮች ዙሪያ ውይይት አካሂደዋል። ረዳት ሚኒስትሩ አሜሪካ በኢትዮጵያ ተግባራዊ ያደረገቻቸውን የትምህርት መርሃ ግብሮችና መንግስት ወጣቱን አስመልክቶ እያከናወናቸው ላሉ ስራዎች ድጋፏን አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል። ቲቦር ናጊ ከትናንት በስቲያ አገራቸው በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መስክ ያላት ትብብር በሚጠናከርበት ሁኔታ ላይ ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የስራ ኃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል። በውይይታቸውም በኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ስላሉ ፈተናዎችና ዕድሎች እንዲሁም የሁለቱን አገራት ዩኒቨርሲቲዎች የጥናትና ምርምር ትስስር ማጠናከር ላይ መምከራቸውም ተገልጿል። ቲቦር ናጊ የኢትዮጵያና አሜሪካን ለ70 ዓመታት ያህል በትምህርት መስክ የዘለቀ ግንኙነት አድንቀዋል። ረዳት ሚኒስትሩ በአሜሪካና በአፍሪካ ዩኒቨርስቲዎች መካከል ያለውን ግንኙነት ማጠናከርና ተቋማቱ ለአገር ልማት አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ድጋፍ በሚያደርገው የአሜሪካ "የዩኒቨርሲቲ ፓርትነርሺፕ ኢኒሼቲቭ" መርሃ ግብር ዙሪያ ከሚኒስቴሩ የስራ ኃላፊዎች ጋር መወያየታቸውንም መግለጫው አትቷል። የአሜሪካ አፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ቲቦር ናጊ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ በዴሞክራቲክ ኮንጎ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳንና ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ጉብኝት አድርገዋል። ቲቦር ናጊ ባለፈው ዓመትም በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወቃል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም