ሐረር ወደ ቀድሞ ሰላሟ ተመለሰች

79
ሐረር ኢዜአ ጥር 19 ቀን 2012፡- ሐረር ከተማ ወደ ቀድሞ ሰላማዊ እንቅስቃሴዋ መመለሷን ፖሊስ አስታወቀ። የሐረሪ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር ረማዳን ኡመር እንደገለጹት የተደራጁ ቡድኖች በአካባቢው የጥምቀት በዓልን አጋጣሚ ተጠቅመው ችግር ፈጥረው ነበር። ተከባብሮ እየኖረ ያለውን ህዝብ አንድነቱን ለመሸርሸርና በዓሉን ለመረበሽ አቅደው የነበረ ቢሆንም የአካባቢው ህብረተሰብ ከጸጥታ አካላት ጋር በተከናወነው ስራ ችግሩ ሳይባባስ ሊገታ መቻሉን ተናግረዋል። ተዘርፈው ከነበሩ 17 ተሽከርካሪዎች መካከል 13 ማስመለስ መቻሉን ጠቁመዋል። ለጥፋት ለማዋል የተዘጋጁ የተለያዩ የጦርና የስለት መሳሪያዎች ፣ እንዲሁም የተዘረፉ የቤት ንብረቶችም በወቅቱ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ኮሚሽነሩ አመልክተዋል። " በአሁኑ ወቅትም ሐረር ወደ ቀድሞው ሰላማዊ እንቅስቃሴ ተመልሷል "ብለዋል። ከከተማዋ ነዋሪዎች መካከል አቶ በቀለ ነጋሽ በሰጡት አስተያየት አሁን በሐረር አንጻራዊ ሰላም ቢኖርም በአንዳንድ አካባቢዎች የጸጥታ ስጋት መኖሩን ተናግረዋል። " የጸጥታ ኃይሉ በዚህ ላይ መስራት አለበት "ብለዋል። ወጣት ቤተልሄም ካሳ በበኩሏ በአካባቢው የጸጥታ ኃይል በሌለባቸው አካባቢዎች አልፎ አልፎ የጸጥታ ችግር እንደሚስተዋል ገልጻለች። የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር በበኩላቸው የጸጥታ ስጋት ባለባቸው አካባቢዎች የተጠናከረ ጥበቃ እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል። እንደ ኮሚሽነሩ ገለጻ በክልሉ ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥም ህዝቡ ከጸጥታ ኃይሉ ጋር በመሆን መስራት ይጠበቅበታል። በአካባቢው በጥምቀት በዓል ወቅት ሁከት ፈጥረዋል ተብለው የተጠረጠሩ 87 ሰዎች መያዛቸውን ኢዜአ ቀደም ብሎ ዘግቧል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም