የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የግል ንጽህናን መጠበቅ ይገባል...ዶክተር ጆን ንኬንጋሶን

52

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 19/2012 የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የግል ንጽህናን መጠበቅ እንደሚገባ የአፍሪካ የበሽታ መቆጣጠር ማዕከል አሳሰበ።

የማዕከሉ ዳይሬክተር ዶክተር ጆን ንኬንጋሶን በሰጡት መግለጫ፣ ቫይረሱ ከእንሰሳት ወደ ሰው የተላለፈ መሆኑን ገልጸው ምከንያቱ ግን ገና አልታወቀም ብለዋል።

በአፍሪካ በበሽታው የተጠቃ ሰው እስካሁን ባይኖርም የተለያዩ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን በኮትዲቯር መከሰቱን ሲዘግቡ መቆየታቸው ተገልጿል።

አሁን ላይ ደግሞ አራት ኢትዮጵያዊያን በኮሮና ቫይረስ ተጠርጥረው ክትትል እየተደረገባቸው መሆኑን የኢፌዴሪ የጤና ሚኒስቴር ገልጿል።

የአፍሪካ የበሽታ መቆጣጠር ማዕከል ዳይሬክተር ዶክተር ጆን ንኬንጋሶን እንደሚሉት ለቫይረሱ እስካሁን የተገኘ መድሃኒት ወይም ክትባት የለም።

በመሆኑም የአፍሪካውያን ቅድመ መከላከል ላይ እንዲያተኩሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የግል ንጽህናን በእጅን በሳሙና መታጠብና አስፈላጊውን የህክምና ምክረ-ኃሳቦችንም መተግበር ይገባል ብለዋል።

ዜጎች ከጉንፋን ጋር የሚመሳሰል የጤና እክል ሲጀምራቸውና ሲያስነጥሱ በስካርፍ ወይም በሶፍት ተሸፍነው መሆን እንዳለበትም መክረዋል።

በሽታው ጫናው ከበረታ አስፈላጊውን ህክምና አንዲያገኙ ወደ ጤና ተቋማት መሄድ አንዳለባቸው ገልጸዋል።  በቻይና 'ሁዋን' ግዛት የተቀሰቀሰው ኮርኖ ቫይረስ እስካሁን 106 ቻይናዊያንን ገድሏል።

በተለያዩ የዓለም አገራት በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች ቁጥርም ከነበረው አሃዝ 60 በመቶ እየጨመረ አሁን ላይ 4 ሺህ 515 ደርሷል።

የአሜሪካው የበሽታ መቆጣጠር ማዕከል የአሜሪካ ዜጎች የቻይና ጉዟቸውን እንዲስርዙ አሳስቧል።

በአሁኑ ወቅት ታይላንድ 14 ሰዎች፣ ሆንግ ኮንግ 8፣ አሜሪካ፣ ታይዋን፣ አውስትራሊያና ማካው ደግሞ እያንዳንዳቸው አምስት ዜጎቻቸው በቫይረሱ ተጠቅተዋል።

ሲንጋፖር፣ ጃፓን፣ ደቡብ ኮሪያና ማሌዥያ ደግሞ እያንዳንዳቸው አራት ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ በፈረንሳይም በሦስት ሰዎች ላይ ተገኝቷል።

በካናዳና ቬትናም ሁለት፤ ኔፓል፣ ካምቦዲያና ጀርመንም እያንዳንዳቸው አንድ አንድ በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች መኖራቸው ተረጋግጧል።

አሁን ከቀትር በኋላ የወጡ መረጃዎች እንደሚያመላክቱት በጃፓን ወደ ቻይና ያልገባ አንድ ግለሰብ በቫይረሱ መያዙ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም