ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ተማሪዎች ትምህርታቸው ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ አሳሰቡ

104

አዲስ አበባ፤ ጥር 19/2012 (ኢዜአ) ተማሪዎች ትምህርታቸው ላይ ብቻ ትኩረት በማድረግ የተሻለ ውጤት ለማምጣት እንዲተጉ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው አሳሰቡ።

በቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት በ13 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ወጪ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ወጫሌ ወረዳ የተገነባው የኢፋ ሰላሌ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ዛሬ በይፋ ተመርቋል።

የትምህርት ቤቱ ግንባታ ሰኔ 2011 ዓ.ም ተጀምሮ በሶስት ወራት የተጠናቀቀ ሲሆን ባለፈው መስከረም  አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።

በ28 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈው ትምህርት ቤቱ 16 የመማሪያ ክፍሎች፣ አንድ የሙያ ማሰልጠኛ ህንጻ፣ የአስተዳደር ቢሮዎች፣ ቤተ-መጽሃፍት፣ ቤተ-ሙከራና ሌሎችም ክፍሎች አሉት።

ትምህርት ቤቱ አሁን ባለበት ሁኔታ 800 ተማሪዎችን የማስተናገድ አቅም ያለው ሲሆን ለማስፋፊያ የሚሆን በቂ ቦታም ተዘጋጅቶለታል።

ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ ትምህርት ለአንድ አገር ሁለንተናዊ ዕድገት ስላለው ከፍተኛ ሚና ገልጸዋል።

ጽህፈት ቤታቸው የአገሪቷን የትምህርት ሽፋን የተሻለ ለማድረግና ተማሪዎች ረጅም ርቀት ሳይሄዱ በአቅራቢያቸው ትምህርት እንዲያገኙ በትኩረት እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

በየአካባቢው የሚገነቡ ትምህርት ቤቶች የተማረ የሰው ኃይል ለማፍራት ታስበው እንደመሆኑ ተማሪዎች ትምህርታቸው ላይ ብቻ በማተኮር ለለውጥ እንዲተጉም አሳስበዋል።

ትምህርት ቤቶችን በአግባቡ መያዝ የሁሉም ሃላፊነት በመሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎችም የድርሻቸውን እንዲወጡ አደራ ብለዋል።

ተማሪዎችና የአካባቢው ነዋሪዎችም ቀደም ሲል በአቅራቢያቸው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ባለመኖሩ ልጆቻቸውን ረጅም ርቀት ልከው የማስተማር አቅሙም ፍላጎቱም እንዳልነበራቸው ገልጸዋል።

በዚህ የተነሳ በርካታ ተማሪዎች የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ሳይጨርሱ ለማቋረጥ እንደሚገደዱም ነው የተናገሩት።

በአቅም ውስንነት ምክንያት የስንቅና የትራንስፖርት ወጪን ጨምሮ የትምህርት ቁሳቁሶችን ማሟላት እንደማይችሉ ገልጸው የትምህርት ቤቱ ግንባታ እፎይታ ፈጥሮልናል ብለዋል።

የቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት በመላ አገሪቷ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን እያስገነባ ሲሆን የኢፋ ሰላሌን ጨምሮ እስካሁን አምስት ትምህርት ቤቶች ተገንብተው ወደ ስራ ገብተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም