በአማራ ክልል አንድ ቢሊዮን 700 ሚሊዮን ችግኞችን ለማዘጋጀት እየተሰራ ነው

57
ጥር፣ 19/2012 (ኢዜአ) በመጪው የክረምት ወቅት ለተከላ የሚበቃ አንድ ቢሊዮን 700 ሚሊዮን ችግኞችን ለማዘጋጀት እየተሰራ መሆኑን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ገለጸ። የሚዘጋጁት ችግኞች በአያያዝና አጠቃቀም ጉድለት የተራቆቱ አካባቢዎችን በደን መልሶ ለመተካት ይውላሉ። በቢሮው የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም ዳይሬክተር አቶ ጌታቸውን እንግዳየሁ ለኢዜአ እንዳሉት ህዝቡን በባለቤትነት በማሳተፍ ባለፉት 11 ዓመታት የችግኝ ተከላና እንክብካቤ  ሲካሄድ ቆይቷል። በዚህም  የክልሉ የደን ሽፋን ከነበረበት 7 በመቶ ወደ 14 ነጥብ 7 በመቶ ማድረስ ተችሏል። ያለፉትን ዓመታት መልካም ተሞክሮ በመጠቀም በመጪው ክረምት ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት እየተሰራ መሆኑን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል። ካለፈው ወር ጀምሮ በ54 ሺህ  የችግኝ ጣቢያዎች የተለያየ ዝርያ ያላቸውን ችግኞች የማፍላት ስራ እየተከናወነ መሆኑን አመልክተዋል። 46 ሺህ የችግኝ ጣቢያዎች  ደግሞ እስከ ተያዘው  ወር መጨረሻ ወደ ማፍላት ይገባሉ። እየተዘጋጁ ያሉት ችግኞችም በመጪው የክረምት ወቅት ከ300 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ የተመረጡ ቦታዎች ይተከላሉ ተብሏል። አርሶ አደር አማረ ላቀ በምዕራብ ጎጃም ዞን ሰከላ ወረዳ የኮለል ለቻ ቀበሌ  ነዋሪ  ሲሆኑ ባለፈው ዓመት ከአዘጋጁት ችግኝ 50 ሺህ ያህሉ  ለምነቱ በተሟጠጠ ማሳቸው አካባቢ መትከላቸውን ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል። የተከሉትን እየተንከባከቡ መሆናቸውንና ቀራቸውን ችግኝም ለአካባቢው አርሶ አደር በመሸጥ 10 ሺህ ብር የሚጠጋ ገቢ እንዳገኙም አመልክተዋል። በያዝነው የበጋ ወራትም ሁለት ሚሊዮን ችግኝ ለማፍላት መዘጋጀታቸውንም ጠቁመዋል። "ሳናውቅ ያወደምነውን ደን መልሰን መተካት ውዴታ ሳይሆን ግዴታችን ነው" ያሉት ደግሞ በዚሁ ወረዳ የአባይ ሳንግብ ቀበሌ አርሶ አደር አበሻ መኮንን ናቸው። እንደ አርሶ አደሩ ገለጻ ቀደም ሲል በግማሽ ሄክታር መሬት የተከሏቸው የዛፍ ችግኞች እየተንከባከቡ ነው፤ በክረምቱ የሚተከል  8 ሺህ ችግኞችን እያዘጋጁ ይገኛሉ። በክልሉ ባለፈው የክረምት ወቅት በአረንጓዴ አሻራ ቀንና በመደበኛው  መርሃ ግብር ከተተከሉት አንድ ቢሊዮን 500ሚሊዮን  ችግኞች ውስጥ 80 በመቶው መጽደቃቸውን ከግብርና ቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም