ኢትዮጵያ፣ ኤርትራና ሶማሊያ ሽብርተኝነትን ጨምሮ ሌሎች ችግሮችን በጋራ ለመከላከል የሚያስችል እቅድ አወጡ

61
ኢዜአ ፤ጥር 18/2012 ኢትዮጵያ፣ ኤርትራና ሶማሊያ ለቀጣዮቹ ዓመታት ሽብርተኝነትን ጨምሮ ሌሎች የጋራ ችግሮችን ለመከላከል የሚያስችላቸው የትግብራ እቅድ ማውጣታቸው ተነገረ። ሶስቱ አገራት በ2010 ዓ.ም የፈረሙትን የሶሰትዮሽ ስምምነት ለማስፈጸም በቁርጠኝነት እንደሚሰሩም አስታውቀዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ከኤርትራ ፕሬዚዳት ኢሳያስ አፈወርቂና ከሶማሊያ ፕሬዚዳንት መሐመድ አብዱላሂ ጋር የሶስትዮሽ ውይይት ለማድረግ ትናንት አስመራ መግባታቸው ይታወቃል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለ አገራቱ አበይት ጉዳዮች እና የአፍሪካ ቀንድ ክንውኖች ላይ ከሁለቱ አገራት መሪዎች ጋር ተወያይተዋል። ከውይይቱም በኋላ ሶስቱ አገራት በ2012 ዓ.ም እና ለቀጣይ ዓመታት የጋራ የሽብር ስጋቶችን ለመከላከል፣ የሕገ-ወጥ የሰዎች፣ የመሣሪያ እንዲሁም የአደንዛዥ ዕጽ ዝውውርን ለመግታት የሚያስችል የትግበራ መርሃ ግብር ማውጣታቸውን ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል። የኢትዮጵያ፣ኤርትራና ሶማሊያ መሪዎች ጳጉሜን 1 ቀን 2010 ዓ.ም በአስመራ አገራቱ በፖለቲካ፣ በማህበራዊ፣ ባህል፣ በኢኮኖሚና ደህንነት ያላቸውን ትብብር ማጠናከር የሚያስችላቸውን የሶስትዮሽ ስምምነት ፈርመው እንደነበር የሚታወስ ነው። ስምምነቱ ቀጠናዊ ሰላምና መረጋጋትን መፍጠር አላማ ያደረገ ሲሆን ስምምነቱን የሚያስፈጽምና የሚያስተባብር በሶስት አገሮች ከፍተኛ አመራሮች የሚመራ ኮሚቴ አቋቁመውም ነበር። የሶስቱ አገራት መሪዎች በዛሬ ውይይታቸው የስምምነቱን አፈጻጸም መገምገማቸውም ተገልጿል። ከውይይቱ በኋላ በአስመራ የፈረሙትን የሶስትዮሽ ስምምነት ለማስፈጸም ያላቸውን ቁርጠኝነት ዳግመኛ ማረጋገጣቸውም ተመልክቷል። የአገራቱ መሪዎች በየአገሮቻቸው ያሏቸውን የሰው እና የተፈጥሮ ሀብቶች ጥቅም ላይ በማዋል የጋራ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ሥራዎችን ለማከናወን መስማማታቸውን ከጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በይፋዊ የፌስቡክ ገፃቸው ከፕሬዚዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ እና ከፕሬዚዳንት መሐመድ አብዱላሂ ጋር ውጤታማ ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል። "በ2010 ዓ.ም የፈረምነውን የሦስትዮሽ ስምምነት ለመፈጸም ያለንን ቁርጠኝነት ዳግመኛ አረጋግጠን ስምምነቶቹን ተግባራዊ ከማድረግ አንጻር የምንገኝበትን የክንውን ሂደት ከልሰናልም"ብለዋል። ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ሥራዎችን ከመከወን በተጨማሪ በቀጠናው ያለውን ሰላም፣ መረጋጋት እና ደህንነት ከማጠናከር አኳያ መግባባት ላይ መደረሱንም ተናግረዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም