ኤጀንሲው የፓስፖርት ፈላጊዎችን መጉላላት ለመቀነስ መስራት ይጠበቅበታል --- የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

154
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 18/2012 የኢሚግሬሽንና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ ከፓስፖርት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ በተገልጋዮች ላይ የሚደርሰውን መጉላላት ለመቀነስ መስራት እንዳለበት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ። የምክር ቤቱ የውጭ ግንኙነትና ሠላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኮሚሽኑን አገልግሎት አሰጣጥ ተመልክቷል። ተቋሙ ከአገልግሎት አሰጣጥ አንጻር ምን ላይ ነው ያለው? የሚያጋጥሙ ችግሮችና መወሰድ ያለባቸው እርምጃዎች ላይ የቋሚ ኮሚቴው አባላት ከኃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል። የቋሚ ኮሚቴው አባላት በተለይ ከፓስፖርት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ በርካታ ቅሬታዎች እየተነሱ መሆኑን ጠቅሰዋል። የፓስፖርት እጥረት እንዲሁም አስቸኳይ ፓስፖርት የሚፈልጉ ተገልጋዮች እስከ 3 ሺህ ብር መጠየቃቸው 'አግባብ አይደለም' ሲሉ ነው የቋሚ ኮሚቴው አባላት ያስገነዘቡት። ተገልጋዮች ፓስፖርት ለማግኘት 75 የሥራ ቀናት መጠበቅ እንዳለባቸው በመመሪያው ቢቀመጥም ዜጎች በተባለው ጊዜ እያገኙ ባለመሆኑ ለእንግልት እየተዳረጉ ነው ብለዋል። እንደ ምክር ቤቱ አባላት ገለጻ ደላሎች በአጭር ጊዜ ፓስፖርት እንድታገኙ እናደርጋለን እያሉ ከተገልጋዮች ገንዘብ እየወሰዱ መሆኑ ተገቢ አይደለም። የኤጀንሲው የሰነድ ምዝገባ ዳይሬክተር አቶ ከድር ሰኢድ በበኩላቸው ለተገልጋዮች የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠጥ ቅርጫፍ የማስፋፋት ተግባራት ሲከናወኑ ቆይተዋል ብለዋል። በስድስት ቦታዎች ላይ ቅርጫፍ መከፈቱን ገልጸው ከእነዚሁ መካከል አዳማ፣ ሰመራና ጅግጅጋን ጠቅሰዋል። እንዲያም ሆኖ ደላሎች በተለይ ክልሎች ላይ የሚሰጠው ፓስፖርት ዋጋ የለውም፣ ዋጋ ያለው አዲስ አበባ የሚሰጠው ነው እያሉ 'ተገልጋዮችን እያደናገሩ ነው' ሲሉ ጠቁመዋል። 'ደላሎችን ከጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር ወደ ሕግ ብናቀርባቸውም ብዙም ሳይቆዩ ይለቀቃሉ' ያሉት ዳይሬክተሩ የሚወሰደው እርምጃ የሚፈለገውን ውጤት እያስገኘ አይደለምና ምክር ቤቱ ያግዘን ብለዋል። ከፓስፖርቱ ዋጋ ጋር ተያይዞ የተነሳው ቅሬታ የዋጋ ተመኑን ያወጣው የገንዘብ ሚኒስቴር መሆኑንና ይህም የሆነበት ምክንያትም ከፍተኛ የፓስፖርት እጥረት በመኖሩ እንደሆነ ተናግረዋል። የፓስፖርት እጥረቱ የተከሰተው ደግሞ ከውጭ እያሳተመ የሚልከው ድርጅት በአግባቡ እየላከ ባለመሆኑ እንደሆነ አስረድተዋል። የቋሚ ኮሚቴው ተወካይ አቶ ጴጥሮስ ወልደሰንበት ኤጀንሲው ፖስፖርት ሙሉ በሙሉ በአገር ውስጥ እንዲመረት የሚያስችሉ ተግባራትን ሊያከናውን እንደሚገባ አሳስበዋል። በተለይም ዘመኑ የደረሰበትን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ረገድ ኤጀንሲው ራሱን ማዘመን እንዳለበትና የሰው ኃይሉን ማብቃት ላይም በትኩረት መስራት እንደሚጠበቅበት አጽንኦት ሰጥተዋል። ቋሚ ኮሚቴው ኤጀንሲው ለሚያከናውናቸው ተግባራት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ገልጸዋል።                
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም